የብልጽግና ጉዟችን ከሁሉም በሁሉም ለሁሉም እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ

You are currently viewing የብልጽግና ጉዟችን ከሁሉም በሁሉም ለሁሉም እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ

AMN ታኀሣሥ 22/2018

የብልጽግና የኢኮኖሚ አቅጣጫ ጉዞ ከሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም እንዲሆን የማድረግ ስራ እንሰራለን ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት በመደመር ፍልስፍና የሚመራው የመደመር መንግሥት በአራት ኢኮኖሚያዊ ሚናዎች ላይ አተኩሮ ይሰራል።

በዚህም የመጀመሪያው ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫን መተግበር መሆኑን አንስተው፤ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት፣ ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልጽግናን የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ብዝሃ ተዋናይ አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸው፤ በኢኮኖሚ ውስጥ ሚና ያላቸው አካላት የተናጠል እና የጋራ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት መንግሥት ግንባር ቀደም ሚናውን እንደሚወጣ ጠቅሰው የግል ዘርፉ በማይሳተፍባቸው ዘርፎች መንግሥት ንቁ ኢንቨስተር እንደሚሆን አስረድተዋል።

ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፎች ያሉ አቅሞችን የመለየት፣ አቅሞቹን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን ስልት መቀየስ እና አቅሞችን ለመጠቀም የሚያስችሉ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መከተል ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በአይሲቲ፣ በማዕድን፣ በግብርና ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ውጤት መምጣቱን አብራርተዋል።

ሦስተኛው ብዝኃ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ አቅጣጫ እንደሆነ ያነሱት አቶ አደም ኢኮኖሚው ሁሉም በፍትሃዊነት የሚጠቀምበት እና የሚሳተፍበት እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህም ለሁሉም እኩል እድል በመፍጠር ተሳትፎውን እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማፋጠን ከውጤቱ ሁሉም በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ በመፍጠር የብልጽግና ጉዟችን ከሁሉም በሁሉም ለሁሉም የሆነ እንዲሆን የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በአራተኛ ደረጃ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን የማጠናከር አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸው፤ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚቻለው ከሌሎች ጋር በመተባበር መሆኑን መግለጻቸውን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

በኢኮኖሚ መተሳሰር፣ በጋራ ጥቅም ዙሪያ በጋራ መስራት፣ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር እንዲሁም ፍትሃዊ ስርዓት እንዲኖር እና የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም ገበያ የተሻለ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል በትብብር መስራት ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review