የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐግብር ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ፡፡ ማንችስተር ሲቲ ወደ ስታዲየም ኦፍ ላይት አቅንቶ ሰንደርላንድን ምሽት 5 ሰዓት የሚገጥምበት ጨዋታ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ጨዋታው በተለይ ለሲቲ ወሳኝ ነው፡፡ አርሰናል አስቶንቪላን በጥሩ ብቃት አሸንፎ ከሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩት በአምስት አስፍቶታል፡፡ የፔፕ ቡድን ልዩነቱን ወደ ሁለት አጥቦ አርሰናል አንገት ስር ለመተንፈስ በዛሬ ምሽት ጨዋታ ሦስት ነጥቡን ማሳካት አለበት፡፡
ነገሮች ግን ለሲቲ ቀላል አይሆንም በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሪጅስ ለ ብሪስ እየተመሩ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ የተመለሱት ሰንደርላንዶች በሜዳቸው ሽንፈት አልገጠማቸውም፡፡
የሊጉ መሪ አርሰናልን ጨምሮ ዘጠኝ ቡድኖች በስታዲየም ኦፍ ላይት ተጫውተው አንዳቸውም በድል አልተመለሱም ፡፡ አምስቱ ተረተው አራቱ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ማንችስተር ሲቲ ሰሞኑን ቢሻሻልም በውድድር ዓመቱ የተረታቸው ሦስቱም ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ የመጡ ናቸው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ በኢትሃድ ተገናኝተው ሲቲ ብዙም ሳይቸገር 3ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በሌላ ጨዋታ ቶማስ ፍራንክ ቶተንሃም ሆትስፐርስን ይዘው ታሪክ ወደ ሰሩበት ጌትች ኮሚኒቲ ስታዲየም በመጓዝ የቀድሞ ክለባቸው ብሬንትፎርድን ምሽት 5 ሰዓት ይገጥማሉ፡፡
ሊቨርፑል ሊድስ ዩናይትድን ምሽት 2፡30 በሜዳው አንፊልድ የሚያስተናግድበት ጨዋታም ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት ክሪስታል ፓላስ እና ፉልሃም የለንደን ደርቢ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ