በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት ይኖረዋል

You are currently viewing በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት ይኖረዋል

AMN ታኅሣሥ 25/2018

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀጣይነት እንዳለው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኤኤምኤን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሰሜን፣ ምስራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ሀገራችን የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እንደሚቀጥል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።

በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በሌላ በኩል ከሚጠናከሩ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች በመነሳት በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ አነስተኛ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቋል።

ዝናብ ሰጪ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውም ገልጿል።

በአብዛኛዎቹ የመኸር አብቃይ አካባቢዎች ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ የሚጠበቅ ሲሆን በተወሰኑ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስታውቋል።

የሚኖረው የበጋው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ በመከናወን ላይ ለሚገኘው የድህረ ሰብል ስብሰባ ስራዎች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ይጠበቃል ብሏል።

በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በጥቂት የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ በሚገኙ ተፋሰሶች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የተሻለ የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ነው ያመላከተው።

በሌላ በኩል የተቀሩት አብዛኛዎቹ የሀገራችን ተፋሰሶች በበጋው ደረቅ የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ ስር እንደሚቆዩ ይጠበቃል ሲልም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review