ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራን ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ለኢንተርፕራይዞች ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባለቻ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ አዘጋጅነት “የኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት ለአዲስ አበባ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው የነባር ኢንተርፕራይዞች ንቅናቄ የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።
ንቅናቄው በዋናነት ነባር ኢንተርፕራይዞች በየደረጃው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመለየት እና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ያሉባቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችል መደላድልን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መንግስት ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጓል ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም ለኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፉ ተጨባጭ ድጋፍን እያደረገ ነው ብለዋል።
ድህነትን ማሸነፍ የምንችለው የስራ አጥ ቁጥርን ስንቀንስ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፤ ለዘርፉ ስኬታማነት ኢንተርፕራይዞችም የጠራ ግብን ይዘው በትጋት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በስራ እድል ፈጠራው በመንግስትና ህዝብ ትብብር አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ሲሆን ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ኢንተርፕራይዞች መንግስት ለመስኩ የሰጠው ትኩረት የሚመሰገን መሆኑን ገልጸው በተለይ ከብድር አገልግሎት እንዲሁም ከገበያ ትስስርና ከግብአት አቅርቦት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ከኢንተርፕራይዞች ለተነሱ ሐሳቦች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ከተማ አስተዳደሩ ምርታማነትን ለማሳደግና የስራ እድል ፈጠራን ለማጎልበት በፖሊሲ የተደገፈ ስራን ከማስራት ባሻገር ለኢንተርፕራይ ዘርፉ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ከብድር አቅርቦት ጋር በታያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከስኬት ባንክ ጋር የፋይናንስ ስርአቱን በጠበቀ አግባብ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የገበያ ትስስርና በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታትም ከከተማ አስተዳደሩ ባሻገር በፌደራል ደረጃም ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢንተርፕራይዞች ከራሳቸው አልፈው ለሐገር የሚጠቅሙ ተቋማት እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ በዘርፉ የተያዘው ውጥን ግቡን እንዲመታ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በሔኖክ ዘነበ