የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ሀይሎች እና ፖሊስ ሠራዊት ማህበራት ህብረት ”የባህር በራችን ለኢትዮጵያችን” በሚል መሪ ቃል የ3ኛ ዓመት ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዷል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በምታደርገው ጥረት የሚጠየቀውንና የሚጠበቅብንን አስተዋፅኦ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን ሲልም የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
መግላጫው መላው ኢትዮጵያዊያን ዘር፣ጎሳና ሀይማኖት ሳይለያየን ጥያቄው እንዲሳካና ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በአስተማማን ሁኔታ እንድታስከብር በአንድነት እንቆም ዘንድ ለትውልዱ ጥሪ እናስተላልፋለን ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግስት ያነሳውን የባህር በር ጥያቄ የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ሀይሎች እና ፖሊስ ሠራዊት ማህበራት ህብረት በፅኑ እንደግፋለን ሲልም ህብረቱ ገልጿል፡፡

ይህ ትውልድ በቁጭት በመነሳት ኢትዮጵያ ያነሳቸው የባህር በር ጥያቄ ወደ ተፈጥሯዊ ህጋዊ መብቷ እንድትመለስ አለም ዓቀፋዊ ዲፕሎማሲ ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑ የ130 ሚሊዮን ህዝብ ጥያቄ እውን እንዲሆን መላው ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም ይገባናል ብለዋል፡፡
ጀግናው ሠራዊታችን የላቀ ወታደራዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በመታጠቅ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ በማፋጠን በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤና የፓናል ውይይት ላይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍንን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊት ተወካዮች፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሀይሎች የሠራዊት ጀኔራል መኮንኖች፣ የፖሊስ ሠራዊት መኮንኖች፣ የህብረቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸዉን ከሃገር መከላከያ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።