አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፦ ከዜና ባሻገር ለወገን ደራሽነት፤ የማዕድ ማጋራት አርአያነት!

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፦ ከዜና ባሻገር ለወገን ደራሽነት፤ የማዕድ ማጋራት አርአያነት!

አዲስ አባባ — ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሚዲያው ስራ ባሻገር በትውልድ ግንባታ እና ማህበራዊ አገልግሎት ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህ ማሳያ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጥቂት የማይባሉ የነገ ሀገር ተራክቢ ህጻናትን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡  ለእነዚህ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት በተጨማሪ ቤጊዜው አልባሳትን በመለገስ አርዓያነት ያለውን ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ  ለህጻናት ቤተሰቦች  በየወሩ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በየአመት በዓላም የማዐድ ማጋራት መርሃ ግብር ያከናውናል፡፡  የ2018 የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ተመሳሳይ የማዐድ አጋርቷል፡፡

 አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (AMN)፣ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት አካል የሆነ “የማዕድ ማጋራት” መርሐ ግብር አከናወነ። ተቋሙ ይህንን ድጋፍ ያደረገው ዘወትር ድጋፍ ለሚያደርግላቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ሲሆን፣ ዓላማውም በዓሉን ያለ ችግርና በደስታ እንዲያሳልፉ ለማስቻል ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎር ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የሬዲዮ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ዛህራ ሰይድ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከ20 በላይ ለሚሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉም በዓሉን አስመልክቶ የቀረበ የአልባሳትና የገንዘብ ስጦታን ያካተተ ነው ብለዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ይህ ድጋፍ የሚከናወነው በተቋሙ ሠራተኞች ሙሉ ፈቃደኝነት መሆኑን ገልጸዋል። የAMN ሠራተኞች ከወርሃዊ ደሞዛቸው አንድ በመቶ (1%) በመቀነስ ለእንደዚህ ያሉ የበጎ አድራጎት ተግባራት እንዲውል ማድረጋቸው፣ ተቋሙ ከመረጃ አቅራቢነት ባለፈ ለዜጎች ያለውን ጥልቅ ማኅበራዊ ተቆርቋሪነትና አጋርነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ እንደማንኛውም ዜጋ በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ተቋሙ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች በሰጡት አስተያየት፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በየዓመቱና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያደርግላቸውን ድጋፍ አድንቀዋል። በተለይም በበዓላት ወቅት የሚደረግላቸው እንዲህ ያለው የማዕድ ማጋራት፣ እንደማንኛውም ዜጋ በራሳቸው ቤት በዓሉን በደስታና በተሟላ ስሜት እንዲያከብሩ ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ተጠቃሚዎቹ “እንዲህ ያለው እርስ በእርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በኅብረተሰቡ ውስጥ ጎልብቶ ሊቀጥል ይገባል” በማለት፣ በተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ላይ ያላቸውን ምስጋና በደስታ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተለመደ የመጣው የመረዳዳትና የማዕድ ማጋራት ተግባር፣ በዜጎች መካከል ያለውን አብሮነትና ወንድማማችነት ከማጠናከሩ ባሻገር፣ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያለባቸው ወገኖች በዓላትን በከፍተኛ የመገለል ስሜት እንዳያሳልፉ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የትውልድ ድምፅ” በመሆን ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ከማድረስ ባሻገር፣ እንደዚህ ያሉ ሰብዓዊ ተግባራትን በማከናወን ለሌሎች የመንግሥትና የግል ተቋማት አርአያነቱን እያስመሰከረ ይገኛል። ተቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በሰዐቱ ተገልጿል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review