እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ! – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ! – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ዘንድሮ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የምናከብረው የተነገረው የተስፋ ቃል መድረሱን፣ የለውጥ ብርሃን መፈንጠቅ መጀመሩን፣ የመሻገር ዘመን መቅረቡን እያመንን ነው። ጉዟችን በውጣ ውረድ የተሞላ ነበር፤ ተስፋ አስቆራጭ መከራዎችን አስተናግደናል። ከእንግዲህ ፈተናው ጨርሶ አይጎበኘንም ባንልም፣ ተስፋችን የሚወለድበት የዋዜማው ዕለት ላይ ደርሰናል። የፍዳው ዘመን ላይመለስ ተሸኝቶ፣ የማንሠራራት ዘመን እንደመጣ በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትናንትን የዋጀ፣ ነገን የታደገ ነው። ከአዳም እስከ ክርስቶስ ልደት የተከናወነው ሁሉ ዋጋ ያገኘው በክርስቶስ መወለድ ምክንያት ነው። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው የሰው ልጅ ሕይወት ቀና የሆነው በክርስቶስ ምክንያት ነው። ክርስቶስ በትናንትና በነገ መካከል “ዛሬ” ሆኖ ሁለቱን አስታርቋቸዋል። ለዚህ ነው የክርስቶስን መወለድ በታላቅ ክብር የምናከብረው።

ክርስቶስ ባይወለድ ኖሮ ትንቢት የተናገሩ ነብያት፣ መሥዋዕት ያቀረቡ ካህናት፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉ አበው፣ ተስፋ ያደረጉ የሰው ልጆች ሁሉ ሥራቸው ታሪክ ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር። ዋጋ ከፍሎ ህያው ያደረጋቸው ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ባይወለድ ኖሮ የሰው ልጅ ወደፊት የሚያከናውናቸው የሥልጣኔ፣ የጽድቅ እና የበጎነት ሥራዎች ሁሉ የድኅነት ቅኝት አይኖራቸውም ነበር። ትናንትን የቀደሰው፤ ነገንም የዋጀው፣ ዛሬ የተወለደው ክርስቶስ ነው።

ይሄንን ታላቅ ትምህርት እናስተውል ዘንድ ይገባናል። ትናንት የቱንም ያህል ታላቅ ታሪክ፣ ታላቅ ቅርስ እና ታላቅ ዕሴት ቢኖረንም ዛሬያችን ከተበላሸ ዋጋ የለውም። ባቢሎን እና ፋርስ፣ አቴና እና ሮም፣ ሱሜር እና ሜሶፖታምያ – ዛሬ በጥንቱ ክብራቸውና ታላቅነታቸው የሉም። እነርሱ ትናንት ነበራቸው። ያጡት ዛሬን ነው። ዛሬን በማጣታቸው ደግሞ ትናንታቸው ትዝታ፣ ነጋቸው ሕልም ሆኗል። ትውስታ እንጂ እመርታ የላቸውም።

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነበረች። የታላላቅ ሥልጣኔዎች ሀገር ነበረች። የታላላቅ መንግሥታትና የታላላቅ ሕዝቦች ሀገር ነበረች፤ የታላላቅ ባህሎች እና የአስደናቂ ቅርሶች ሀገር ነበረች። ጥያቄው “ዛሬስ” የሚለው ነው። ዛሬ በድህነት፣ በኋላ ቀርነትና በረሃብ የምንሰቃይ ከሆነ፣ ታሪካችንን አልዋጀነውም ማለት ነው። ትናንትን የሚዋጀው ዛሬ ነውና። ትናንት የሚቃኘውና የሚተረጎመው በዛሬ መንፈስ ነው። የዛሬ ከፍታ ትናንትን ጨምሮ ከፍ ያደርገዋል። የዛሬ ተዋርዶ ደግሞ ትናንትን ጨምሮ ያወርደዋል።

የሀገራችንን ታላቅነት የሚገነዘብ ትውልድ አሁን ተፈጥሯል፡፡ ትውልዱ የድህነትን በትር ደጋግሞ ቀምሷል፤ የኋላቀርነትን አስቀያሚ መልክ እስኪበቃው አይቷል፡፡ የትናንት ስሕተት ያስከተለውን ፍዳ ትከሻው እስኪጎብጥ ለመሸከም ተገድዷል፡፡ የመልክአ ምድር እሥረኝነት ዓይን አፍጥጦ፣ ጥርስ አግጥጦ ሲመጣ የታዘበ ትውልድ ነው፡፡ የችግሩን ልክ መዝኖ መረዳት ብቻ ሳይሆን የመሻገሪያ መርከቡን መገንባት የሚያውቅ ትውልድ ነው፡፡ የትናንት ኩስመናን በዛሬ ትጋት እንደሚያሸንፉ የሚያምኑ ዜጎች ቁጥራቸው በጨመረ ቁጥር የነገ ቁመናችን እንደሚሻሻል ጥርጥር የለውም፡፡

የነቢያት ጽድቅና ትንቢት የቀጠለው የነቢያት አምላክ ክርስቶስ ትንቢታቸውን ፈጽሞ ስለተወለደ ነው። የትንቢት መጻሕፍት ዋጋ ያገኙት በወንጌል መጻሕፍት የተነሣ ነው። ብሉይ ኪዳን ጥቅም ያገኘው በሐዲስ ኪዳን ምክንያት ነው። ሁሉንም ትናንቶች የዋጃቸው ዛሬ ነው። ትናንታችን ዋጋ እና ክብር እንዲኖረው ከፈለግን ዛሬ ተግተን እንሥራ። ብዙ ጊዜያችንን በትናንት ትዝታ እና ትውስታ ውስጥ ከምናሳልፍ፣ በዛሬ ትግልና ውጣ ውረድ ላይ እናጥፋ። ዛሬያችን የተስተካከለና የተቃና ከሆነ፣ ያለ ጥርጥር ትናንትናችን ተገቢውን ክብር ያገኛል።

ክርስቶስ ባይወለድ ኖሮ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ዘመን አዲስ ዘመን አይሆንም ነበር። “ነገን ለመተንበይ የተሻለው መንገድ፣ ነገን ራሱን መፍጠር ነው” ይባላል። የሰው ልጆችን ነገ ክርስቶስ ጀመረው፤ ክርስቲያኖች ደግሞ ተራመዱበት። ዛሬ የተሻለ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ነገን የተሻለ አድርገው ይፈጥሩታል። ዛሬን በዋዛና በፈዛዛ፣ በክፋትና በሤራ የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ነገን የባሰ አድርገው ያበላሹታል።

የኢትዮጵያ ነገ በዛሬ ሥራና ተጋድሎ እንጂ በዛሬ ምኞትና መሻት ብቻ አይመጣም። አንዳንዶች የኢትዮጵያን ነገ ለማበላሸት ዛሬ በክፋት ሥራዎች ተነክረዋል። እኛ ግን የኢትዮጵያን ነገ ለማቅናት ስንል ነገን በሚዋጁ ሥራዎች ተጠምደናል። ነገን የሚዋጀው ዛሬ መሆኑን ስለምናውቅ፣ ነገን ተቀምጠን አንጠብቀውም። ሠርተን እንደርስበታለን እንጂ።

ከቤተልሔም በረት እስከ ቀራንዮ ዐደባባይ የሰው ልጆች ትናንት ሲቀደስ፣ የሰው ልጆች ነገ ሲሠራ መልከ ብዙ ምላሽ ነበረው። የተኙ ነበሩ። የናቁ ነበሩ። ገዳዮች ነበሩ። አሳዳጆች ነበሩ። ሤረኞች ነበሩ። ወሬኞች ነበሩ። አደናቃፊዎች ነበሩ። ነቃፊዎች ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ ገብቷቸው የተከተሉ፤ ነገን ለመሥራት የተባበሩ፤ እውነት ለመንገር የደፈሩ፤ ለእውነት ለመሠዋት የቆረጡ፤ ጥቂቶች ቢሆኑም ብዙዎችን ለማፍራት የሚተጉ – ነበሩ።

የኢትዮጵያ ነገ ሲሠራም ምላሹ ልዩ ልዩ ነው። የሚያሸንፉት ግን ተግተው የሚሠሩት ናቸው። ቪክቶር ሁጎ “ጊዜው የደረሰን ሐሳብ ለማስቆም የሚችል ኃይል በዓለም ላይ የለም” ብሎ ነበር። የኢትዮጵያ ብልጽግና ጊዜው የደረሰ ሐሳብ ነው። ማንም ሊያስቆመው አይቻለውም። የኢትዮጵያ ታላቅነት ጊዜው የደረሰ ሐሳብ ነው። ሊገታው የሚችል ምንም ኃይል የለም።

እኛ ዛሬ የቆምነው በትናንት እና በነገ መካከል ነው። ትናንትን በዛሬ ሥራችን ዋጋ እንዲያገኝ እናደርገዋለን። ነገን ደግሞ በዛሬው ሥራችን አሣምረን እንገነባዋለን። የክርስቶስን የልደት በዓል ይሄንን ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እያሰብን እናከብረዋለን።

በድጋሚ መልካም የልደት በዓል ይሁንልን!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ታኅሣሥ 28፣ 2018 ዓ.ም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review