ለ24 አመታት በእግር ኳሱ የቆየውና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ያፈራዉ የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ከ6 እስከ 17 አመት ያሉ ታዳጊዎችን በመያዝ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡
በርካታ ታዳጊዎችን ያፈራው የአስኮ ፕሮጀክት ሜዳም በመደመር ትውልድ መጽሀፍ ሽያጭ ከተሰሩ ሜዳዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል፡፡
የአስኮ ፕሮጀክት ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፣ በከፍተኛ ሊግ ፣ በአንደኛ ሊግ ፣ በታዳጊዎች እና ለወጣት ቡድን ተጫዋቾችን አብቅቷል።

ፕሮጀክቱ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ዘካሪያስ ቱጂን ጨምሮ 14 የሚደርሱ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ማፍራት ችሏል፡፡
መሟላት ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ለመፍጠር ለተወሰኑ ተጫዋቾች ልዩ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆናቸውን የአስኮ ፕሮጀክት አሰልጣኞች ከኤ ኤምኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሜዳዎች አመቺ ባለመሆናቸው ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ተጫዋቾችን ለማፍራት አስቸጋሪ እንደነበር የሚገልፁት አሰልጣኞቹ አሁን ብዙ መሻሻሎች በመኖራቸው ስራውን ቀለል አድርጎልናል ብለዋል፡፡

መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የማዘውተሪያ ስፍራዎች በደንብ ቢስተካከሉ እንደ አስኮ ፕሮጀከረት ከ10 አመት በኋላ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ለማፍራት አቅደናል ሲሉም አሰልጣኞቹ አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እንደ መሰሉ አበራ አይነት ተጫዋቾችን ያፈራው አስኮ ፕሮጀክት አሁን ግን በሴቶቹ ተዳክሞ ታይቷል፡፡
ቡድኑ ውስጥ የተወሰኑ ሴት ተጫዋቾች ቢኖሩም ከወንዶቹ ጋር በመቀላቀል ስልጠና እየወሰዱ ሲሆን በቀጣይ ግን እንደ አዲስ ቡድን ለማቋም በጥረት ላይ መሆናቸውን አሰልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡
በአልማዝ አዳነ