ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ጠቅላይ ሚኒስትራችን በጉባ ካበሠሯቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውንና በአፍሪካ ግዙፉን የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ዛሬ በቢሾፍቱ አስጀምረናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከስምንት ዐሠት ዓመታት በፊት በጥቂት አውሮፕላኖች ጉዞውን ጀመረ። ዓላማው ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር ማገናኘት ብቻ አልነበረም፤ የአፍሪካን ክብር በሰማይ ላይ ከፍ አድርጎ ማሳየት ጭምር እንጂ።
በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ ዐቅም የሚፈጥረው አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኩራት ታሪካችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የኢትዮጵያ ግልጽ ራዕይና የብልጽግና ጉዞ ማሳያ ነው።
ፕሮጀክቱ የመንግሥታችንን በትልቁ አስቦ በትልቁ የማሳካት ዕይታን የሚገልጥ፣ የአፍሪካን የልዕልና ጉዞ በማረጋገጥ በዓለም አቪዬሽን መሪ ሚና እንዲኖራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የአየር መንገዳችንን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ይበልጥ ከፍ የሚያደርገው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳው የላቀ ነው። አየር መንገዳችን ወደ አፍሪካ መግቢያ እና መውጫ ዋናው በር ሆኖ ይቀጥላል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ የፈጠራና ፍጥነት ጉዟችን በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።