የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ “የትውልድ ድምፅ” የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህዝብና መንግስትን በመረጃ በማስተሳሰር የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የጎላ ሚና መጫወቱን ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦለት ተመልክቷል።
በዚህም ሚዲያው ከመልካም አስተዳደር፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከገበያ ማረጋጋት እና በከተማዋ ከተከናወኑ የልማት ስራዎች ጋር ተያይዞ ተከታትሎ በመዘገብ ህዝቡ አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኝ ገንቢ ሚና መጫወቱን ገልጿል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የህዝቡን ጥያቄ ፊት ለፊት በማውጣትና የህዝብ ቅሬታዎች እንዲፈቱ ጉልህ ሚና መጫወቱን ቋሚ ኮሚቴው አብራርቷል።
ሚዲያው የ”24/7″ የሥራ ባህልን ለማስረጽ የጀመራቸውን የአመለካከት ለውጥ ግንዛቤና የወል ትርክትን የመገንባት ሥራዎችን አጠናክሮ ሲሠራ መቆየቱንና የላቀ ለውጥ እያስመዘገበ እንደሚገኝም ተገልጿል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ባለፉት ስድስት ወራት በይዘትና በአቀራረብ ተወዳዳሪ እየሆነ መምጣቱን የጠቀሰው ቋሚ ኮሚቴው፤ ተቋሙ በርካታ ሪፎርሞችን ከመሥራት ጎን ለጎን የመንግስትን የልማት አቅጣጫዎች መሠረት በማድረግ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በአለሙ ኢላላ