የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን ጎበኝተዋል፡፡
በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙት ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች የአዲስ አበባን ዕድገት እና ከፍታ በጉልህ እንደሚያንፀባርቁ በተጠቆመበት የጉብኝት መርሐ-ግብር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከእንጦጦ እስከ አራዳ ፓርክ የተዘረጋውን የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉት የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረው እስኪጠናቀቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።
አክለውም የአካባቢ ጥበቃን እና ሰው-ተኮር ልማትን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘውን ይህን ፕሮጀክት በምሁራን ተጠንቶ እና ተሰንዶ ለትውልድ መተላለፍ አለበት ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ፣ በወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሚናቸው ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በተለያዩ የማማከር እና ሙያዊ ድጋፍ ከዩኒቨርሲቲው ብዙ እንደሚጠበቅ መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።