ባለፉት የለውጥ ዓመታት በገቢዎች ዘርፍ የተከናወኑ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም የማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ገለጹ።
ሚኒስትሯ እንደተናገሩት ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን ለመዘርጋት በተከናወኑ ተግባራት ምክንያት በታክስ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል። በተለይም በ2011 ዓ.ም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ (e-filing) ታክስ የሚያሳውቁ ግብር ከፋዮች 10.1 በመቶ ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ በ2017 ዓ.ም ይህ ቁጥር ወደ 94 በመቶ ከፍ ብሏል። በተመሳሳይ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ግብር የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ምጣኔ በ2017 ዓ.ም 64 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 709 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ256 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው። በበጀት ዓመቱ በጠቅላላው 2.1 ትሪሊየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደውን ግብ ለማሳካት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።
በቀጣይም ቴክኖሎጂ መር የታክስ አስተዳደርን በማጠናከር የታክስ ስወራን መከላከልና በግብር ከፋዩና በታክስ አስተዳደሩ መካከል መተማመንን የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ የኢትዮጵያ “የፋይናንስ እመርታ” ኮንፈረንስ ላይ መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታዉቋል።