የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማንኛውንም ዓይነት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመከላከልና የመቋቋም አቅማችንን በማሳደግ፣ በራሳችን ጥረትና ድካም እየተረዳዳን ለዘላቂ ልማት እንተጋለን ሲሉ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ልመናና ተረጂነት ስንፍናን የሚያስፋፉ፣ ሰብአዊ ክብርን የሚነኩና ዘላቂ ልማትን የማያረጋግጡ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የግድ ይላል። በተለይም የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት ይህንን የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብ በመለወጥ ረገድ ዋነኛ ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ይህንን ተግባር ለማሳለጥ የአዲስ አበባ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት የአደጋ ተጋላጭነትን በማስቀረት፣ የአደጋ ዝግጁነትን በማጠናከርና ምላሽ ሰጪነትን በማሳደግ በኩል እንደ ሀገር የተጀመረውን የአሰራር ለውጥ ለማስቀጠል ዛሬ ስራውን በይፋ ጀምሯል ብለዋል ከንቲባ አዳነች ።
ምክር ቤቱ የተረጂነትን አሉታዊ አስተሳሰብ ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥም ግንባር ቀደም ሚናውን ለመወጣት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡