የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በተገነባው ዘመናዊው የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከል ለሚገኙ አረጋውያን ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማዕድ ማጋራትና የጋቢ ማልበስ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕከት እንደገለጹት መርሐ ግብሩ የተከናወነው ከሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በተገነባው ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያና መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ ነው። በዚህም የአገር ባለውለታ የሆኑና ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን እናትና አባቶች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ተደርጓል።

ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ በልማት ሥራዎቹ ሁሉ አረጋውያንን ታሳቢ ማድረጉን አንስተው፣ ቀሪ ዘመናቸውን በክብርና በደኅንነት እንዲያሳልፉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ስኬት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለተወጣው ለሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከሚፈልጉ ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።