የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ይፋ የተደረገው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዳያስፖራው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከልና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፤ ባንኩ በየወቅቱ አሰራሩን በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ባንኩ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ስራ ላይ የዋለው መተግበሪያ የባንኩን የዲጂታል ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅሰው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ደንበኞችን ይበልጥ የሚያስተሳስርና የሐዋላ ሂደትን የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግረዋል።
መተግበሪያው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ባለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ መተግበሪያውን ከንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ያበለጸገው የስታር ፔይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሱፍቃድ ጌታቸው ገልጸዋል።
መንግስት ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ መሰል ፈጠራዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማበልጸግ እንደሚሰሩ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።