AMN ጥር 14/ 2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር በመሆኗ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ ተገቢ እና ምክንያታዊ መሆኑን የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ቫደፉል (ዶ/ር) ገለጹ::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ቫደፉል (ዶ/ር) ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሮቹ ከውይይቱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሪድሪች ሜርዝ በቡድን-20 የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ያደረጉት ስብሰባ፣ለሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት አዲስ መነቃቃትን መፍጠሩን ገልጸዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ቫደፉል (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር በመሆኗ ጀርመን ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ለጀርመን ኩባንያዎች ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዳላት ጠቅሰው፤ በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ተሳትፏቸውን ይበልጥ እንደሚያሳድጉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም በሶማሊያ ያለውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመደገፍ ረገድ እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
ዮሐን ቫደፉል (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር በመሆኗ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ ተገቢ እና ምክንያታዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ (COP-32) ለማስተናገድ በመመረጧ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የፖለቲካ እና የልማት ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ጀርመን በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንዱስትሪ እና በንግድ ዘርፎች ያላትን ድጋፍ እንድታጠናክር ጥሪ ማቅረባቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ እና ጀርመን 120 ዓመታትን የዘለቀ የቆየና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው አገራት ናቸው።