የተረከዝ ህመም እንዴት ይከሰታል?

You are currently viewing የተረከዝ ህመም እንዴት ይከሰታል?
  • Post category:ጤና

AMN – ጥር 19/2018 ዓ.ም

በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች ከእንቅልፍ ሲነቁ ወይም ለረጅም ጊዜ ተቀምጠው ሲነሱ በተረከዝ አካባቢ በሚሰማ ከፍተኛ ህመም እንደሚቸገሩ ይስተዋላል።

የተረከዝ ህመም በተለያዩ የጤና ምክንያቶች የሚከሰት ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን ከእለት ተእለት የጫማ ምርጫ እና ከእንቅስቃሴ ልምዶች ጋር የተያያዘ እንደሆነ የአጥንት ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ናታን ወንድወሰን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ዶ/ር ናታን እንደገለጹት፤ የተረከዝ ህመም የሚከሰተው በተረከዝ አጥንት እና በዙሪያው ባሉ ህብረ ህዋሳት ላይ ከመጠን በላይ ጫና ሲፈጠር ነው፡፡

በተለይም ከተረከዝ እስከ ጣቶች የሚዘረጋው ህብረ ህዋስ ወይም ፕላንታር ፋሺያ (Plantar Fascia) መቆጣት ለህመሙ ቀዳሚው ምክንያት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የጫማ ገበር በጣም ጠፍጣፋ የሆኑ ወይም ተረከዛቸው የደነደነ ጫማዎችን ማዘውተር፣ ለረጅም ሰዓታት በጠንካራ ወለል ላይ መቆም እና የሰውነት ክብደት መጨመር ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎችም በተረከዝ አጥንት ላይ የሚፈጠር አላስፈላጊ የአጥንት እድገት (Heel Spurs) ለጽኑ ህመም መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ናታን አብራርተዋል።

ይህንን ህመም ለማስታገስ በቤት ውስጥ የሚከናወኑ ቀላል ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡ ዶ/ር ናታን ይመክራሉ።

ለተጎዳው እግር ተገቢውን ዕረፍት መስጠት ቀዳሚው ተግባር ሲሆን፣ ህመም በሚሰማበት አካባቢ በቀን ለሁለትና ለሦስት ጊዜያት በረዶን በጨርቅ ጠቅልሎ ለ15 ደቂቃ መያዝ እብጠትና ህመምን ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል።

በተጨማሪም ጠዋት ከአልጋ ከመውረድ በፊት የእግር ጡንቻዎችንና ጅማቶችን ቀስ እያሉ መለጠጥ (Stretching) ህመሙን በእጅጉ ያቃልላል። እንደ አስፈላጊነቱም በሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ የህመም ማስታገሻዎችና የፊዚዮቴራፒ ሕክምናዎች እንደ አማራጭ እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

የተረከዝ ህመም እንዳይከሰት ወይም ተመልሶ እንዳይመጣ አስቀድሞ መጠንቀቅ ይቻላል የሚሉት ዶክተር ናታን፤ ለተረከዝ ቅርጽ ምቹ የሆኑ፣ ገበሮቻቸው ለስላሳ እና ምቾት ያላቸውን ጫማዎች መጫመት ህመሙን መከላከል እንደሚረዳ አብራርተዋል።

በተለይም በቤት ውስጥ በባዶ እግር ከመሄድ ይልቅ ለስላሳ ነጠላ ጫማዎችን መጠቀም እንደሚገባ ዶ/ር ናታን ይመከራሉ። ከዚህም ባሻገር የሰውነት ክብደትን ማመጣጠን በእግር ላይ የሚደርሰውን ጫና ስለሚቀንስ ለተረከዝ ጤንነት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ህመሙ ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆየ ወይም እግርን መሬት ለማስነካት እስከሚያስቸግር ድረስ ከባድ ከሆነ፣ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ የአጥንት ወይም የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ማማከር እንደሚገባ ዶክተር ናታን ወንድወሰን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review