ሚካኤል አርቴታ ለአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቹ የበለጠ ነፃነት መስጠት ይገባው ይሆን?

You are currently viewing ሚካኤል አርቴታ ለአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቹ የበለጠ ነፃነት መስጠት ይገባው ይሆን?

AMN ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም

አርሰናልን ከዓመት ዓመት በማሻሻል ለዋንጫ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው ያደረገው ሚካኤል አርቴታ ዘንድሮ ዋንጫ ካላነሳ እንደ ውድቀት የሚቆጥሩት በርካታ ናቸው፡፡

የሰሜን ለንደኑ ክለብ የትኛውም ክለብ የሚመኘው ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ በአራት ውድድሮች ጠናካራ ጉዞ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን በሊጉ የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሁለት ብቻ ማሳካቱ ጥርጣሬ የሚያነሱ እንዲበረክቱ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም አርሰናል ባለፉት ጥቂት ዓመታት እዚህ ቦታ ላይ ተገኝቶ አጨራረሱ አላማረም፡፡

ዘንድሮ አስደናቂ የመከላከል ብቃቱ እዚህ ለመገኘቱ ትልቅ ድርሻ ይወስዳል፡፡ እንደ ቡድን ጨዋታ የሚቆጣጠርበት መንገድ እና የማጥቃት ተጨዋቾች ከፊት ጀምረው መከላከሉን ማስጀመራቸው በሊጉ ጥቂት ግብ ብቻ እንዲቆጠርበት (17) ምክንያት ሆኗል፡፡

አርሰናል በማጥቃቱም ቢሆን የሊጉ ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን ነው፡፡ መድፈኞቹ ያስመዘገቧቸው 42 ግቦች ከማንችስተር ሲቲ በመቀጠል ሁለተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ የአርሰናል የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ከሙገሳ ይልቅ እየተቀበሉ ያሉት ወቀሳውን ነው፡፡ አርሰናል በ23ኛ ሳምንት የሊግ መርሐግብሩ በሜዳው ኤምሬትስ በማንችስተር ዩናይትድ ከተሸነፈ በኋላ በተለይ በአጥቂ ስፍራ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ትልቅ መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡

ለበርካታ ሳምንታት የሊጉን መሪነት ለማንም ያላስቀመሱት አርሰናሎች በሊጉ ከአምስት በላይ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች የላቸውም፡፡ በሊጉ ካሉ ከፍተኛ 20 ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾች መሀከል የአርሰናል ተጫዋች የለም፡፡ የክለቡን የዋንጫ ጥም ይቆርጣል ተብሎ የመጣው ቪክቶር ዮኬሬሽ እና ሊአንድሮ ትሮሳርድ አምስት ግብ ላይ የደረሱ ብቸኛ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ዋንጫ የማሸነፍ ጥበቃው ከዘንድሮ እንዲያልፍ ያልፈለገው አርሰናል በክረምት የተጫዋቾች ዝውውር ቪክቶር ዮኬሬሽ ፣ ኖኒ ማዱኤኬ እና ኤብሪቼ ኤዜን አስፈርሞ የማጥቃት ሃይሉን አጠንክሯል፡፡ ተጫዋቾቹ ግን በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ስዊድናዊው አጥቂ ዮኬሬሽ አምስት ፣ ኤዜ አራት የሊግ ግቦችን ሲያስቆጥሩ ኖኒ ማዱኤኬ ግብም አላስቆጠረም ፤ ግብ የሆነ ኳስ ማቀበልም አልቻለም፡፡ በሰሜን ለንደን ደርቢ ሃትሪክ ሰርቶ የአርሰናል ደጋፊዎችን ያስፈነደቀው ኤብሪቼ ኤዜ ግብ ማስቆጠር አይደለም በቂ የመሰለፍ እድል እንኳን እያገኘ አይደለም፡፡ የቀድሞ የክሪስታል ፓላስ ተጫዋች በመጨረሻ ከተከናወኑ ሰባት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሜዳ ላይ የቆየው 55 ደቂቃዎችን ብቻ ነው፡፡

ቀደም ሲል የቡድኑ አለኝታ የነበሩ ተጫዋቾችም የተሻለ ነገር ማሳየት አልቻሉም፡፡ በተለይ እንግሊዛዊው የመስመር አጥቂ ቡካዮ ሳካ በተለያየ ምክንያት በፊት የነበረውን ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን አጥቶታል፡፡ የክለቡ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረው ቡካዮ ሳካ ከ21 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ያገናኘው በአራት አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ ጉዳት እየደጋገመው የሚገኘው ተጫዋቹ በሁሉም ውድድር ካደረጋቸው 13 የመጨረሻ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡

ሌላኛው የአርሰናል ተስፋ ጋብርኤል ማርቲኔሊ በሁሉም ውድድሮች የዘጠኝ ግብ ባለቤት ቢሆንም ፣ በፕሪምየር ሊጉ ያስመዘገበው ግን አንዱን ብቻ ነው፡፡ ከነባሮቹ ተጫዋቾች የተሸለ ቁጥር እያስመዘገበ የሚገኘው ሊአንድሮ ትሮሳርድ በሊጉ አምስት ግቦች ቢኖሩትም ከመጨረሻዎቹ 11 ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሯል፡፡ ማርቲን ኦዴጋርድ ፣ ጋብርኤል ጄሱስ እና ካይ ሀቨርትዝ በጉዳት የሚጠበቅባቸውን መከወን ያልቻሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

አርሰናል የሊጉ መሪ ቢሆንም የማጥቃት ሚና ተጫዋቾቹን አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ በተለይ በክፍት ጨዋታ በርካታ ግብ ያለማስቆጠር ችግሩ ካልተቀረፈ የአርሰናል ተገማችነት ይበልጥ እየሰፋ መጥቷል፡፡ እንደ ቴሌግራፍ ቁጥራዊ መረጃ ከ1-6 ደረጃ ከያዙ ቡድኖች ውስጥ ከክፍት ጨዋታ ጥቂጥ ግብ ያስቆጠረው አርሰናል ነው፡፡ የሰሜን ለንደኑ ክለብ 22 ግቦችን አስመዝግቧል፡፡ በዚህ መለኪያ ቀዳሚ የሆነው ማንችስተር ሲቲ 36 ግቦች አሉት፡፡

በሊጉ ለአርሰናል የመጫወቻ ክፍት ቦታ የሚሰጡ ክለቦች ጥቂት ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት አበርክቶአቸው የገዘፉ የመስመር ተጫዋቾች በበርካታ አጋጣሚ ተፅእኖ ለመፍጠር ይቸገራሉ፡፡ ተጫዋቾቹ የመጫወቻ ቦታ (Space) ሲያገኙ ምን መስራት እንደሚችሉ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አሳይተዋል፡፡ ባየርን ሙኒክ ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ኢንተር ሚላንን በገጠሙባቸው ፈታኝ ጨዋታዎች 10 ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡

የአርቴታው ቡድን ቅፅል ስም እስኪወጣለት ድረስ በቆሙ ኳሶች ላይ ያለውን ጥገኝነት በክፍት ጨዋታዎች ላይም ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች በሲስተም የታጠሩ ብቻ ሳይሆነ ነፃነት አግኝተው ምን መስራት እንደሚችሉ ቢያሳዩ ይመረጣል ይላል የቴሌግራፍ ፅሁፍ፡፡ ሚካኤል አርቴታ ይህን ይፈቅድ ይሆን? ካልቀየረስ በለመደው መንገድ ሄዶ ዋንጫ ያነሳል? በጊዜ ሂደት የሚመለሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review