AMN ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ አዘጋጇ ሞሮኮ እና ሴኔጋል ባደረጉት ጨዋታ የነበረውን ውዝግብ የመረመረው የካፍ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
የተሰጠባቸውን ፍፁም ቅጣት ምት በመቃወም የቡድን አባላት ከሜዳ እንዲወጡ ያነሳሳው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሰልታኝ ፓፔ ቲያው ካፍ የሚያዘጋጃቸውን አምስት ጨዋታዎች እንዳይመራ ታግዷል።
የስፖርታዊ ጨዋነት መርህን ጥሷል የተባለው የ43 ዓመቱ አሰልጣኝ በተጨማሪ የ100 ሺ የአሜሪካ ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል።
የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ኢሊማን ባሮይ ኒዳዬ እና ኢስማኤላ ሳር በዳኛው ላይ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪይ ሁለት የካፍ ጨዋታዎችን ታግደዋል፡፡

የሴኔጋል እግርኳስ ፌዴሬሽን ደጋፊዎች ፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች ላሳዩት ያልተገባ ባህሪ 600ሺ የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል ተበይኖበታል።
በሞሮኮ በኩል አምበሉ አችራፍ ሀኪሚ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ባህሪ በማሳየቱ ሁለት የካፍ ጨዋታዎችን ሲታገድ ፣ ኢስማኤል ሳባሪ በተመሳሳይ ጥፋት ሦስት ጨዋታዎችን አያከናውንም፡፡ ኢስማኤል ሳባሪ በተጨማሪም የ100 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል።
በተጨማሪ ኳስ አቀባይ ታዳጊዎች ፎጣ ለመንጠቅ ላሳዩት ተገቢ ያልሆነ ባህሪ የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን 200 ሺህ ዶላር እንዲከፍልም ተወስኖበታል፡፡
በተጨማሪ የዕለቱ ዋና ዳኛ የድጋሚ ምስል (VAR) ሊመለከቱ በሚያቀኑበት ወቅት የሞሮኮ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይከውኑ እንቅፋት በመሆናቸው ፌዴሬሽኑ ተጨማሪ 100 ሺ ዶላር እንዲከፍል የካፍ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ቅጣት አስተላልፎበታል።
በሸዋንግዛው ግርማ