AMN- ጥር 21/2018 ዓ. ም
የጠፈር ተመራማሪዎች ከመሬት ጋር በመጠንና በይዘት እጅግ በጣም የምትቀራረብ “HD 137010 b” የተሰኘች አዲስ ፕላኔት ማግኘታቸውን አስታወቁ።
በናሳ (NASA) ኬፕለር ቴሌስኮፕ መረጃ አማካኝነት የተገኘችው ይህች ፕላኔት፣ ለሕይወት ተስማሚ በሆነ ቀጠና ውስጥ የመገኘት ዕድሏ 50 በመቶ መሆኑ ለዘርፉ ተመራማሪዎች ትልቅ ተስፋን ሰጥቷል።
በጠፈር ተመራማሪዎች ዘንድ “HD 137010 b” ተብላ የተሰየመችና ከመሬት ጋር ተመሳሳይ መጠን ያላት አዲስ ፕላኔት፣ ከፀሐይ ጋር በሚመሳሰል ኮከብ ዙሪያ ስትሽከረከር መገኘቷ ተበሰረ።
ይህች ፕላኔት ከመሬት 146 የብርሃን ዓመታት ርቃ የምትገኝ ሲሆን፣ ለሕይወት ተስማሚ በሆነ ቀጠና ውስጥ የመገኘት ዕድሏ 50 በመቶ መሆኑን ሳይንቲስቶች ገልጸዋል።
በመጠን ከመሬት 6 በመቶ የምትበልጥ ሲሆን፣ በይዘትም ከመሬት ጋር በጣም ትቀራረባለች ተብሏል።
የአየር ሁኔታና የሙቀት መጠን
ፕላኔቷ በማርስ ላይ ካለው ጋር ተመሳሳይነት ያለው የቅዝቃዜ መጠን ሊኖራት እንደሚችል ተገምቷል። የሙቀት መጠኗም እስከ ነጊቲቭ 70 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊወርድ እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል።
ምንም እንኳን የሙቀት መጠኑ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ሳይንቲስቶች ፕላኔቷ ያሏት ሌሎች አመቺ ሁኔታዎች ለወደፊት የጠፈር ምርምር ትልቅ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ግኝቱ እንዴት ተገኘ?
ከአውስትራሊያ፣ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ እና ከዴንማርክ በተውጣጡ ዓለም አቀፍ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን የተገኘችው ይህች ፕላኔት፣ የሕይወት ምልክት ሊገኝባቸው ከሚችሉ የጠፈር አካላት አንዷ ተደርጋ ተወስዳለች።
ተመራማሪዎቹ ፕላኔቷን ሊለዩ የቻሉት እ.ኤ.አ. በ2017 የናሳው (NASA) ኬፕለር የጠፈር ቴሌስኮፕ “K2” ተብሎ በሚጠራው ተልዕኮው ባሰባሰበው መረጃ አማካኝነት ነው።
በአውስትራሊያ የሳውዘርን ኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ (USQ) ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ቼልሲ ሁዋንግ እንደገለጹት፤ ፕላኔቷ ልክ እንደ መሬት ሁሉ በ355 ቀናት ውስጥ ኮከቧን ትዞራለች። ይህም ከመሬት የሥርዓተ-ፀሐይ መዞሪያ ጊዜ ጋር በጣም የተቀራረበ ያደርጋታል።
ከሌሎች ፕላኔቶች የሚለያት ባህሪ
ፕላኔቷን ልዩ የሚያደርጋት፣ የምትዞረው ኮከብ (ፀሐይ) ከእኛ የሥርዓተ-ፀሐይ ርቀት 146 የብርሃን ዓመታት ያህል መራቋ ነው ሲሉ የጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት ሁዋንግ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በፀሐይ መሰል ኮከብ ዙሪያ ለሕይወት አመቺ በሆነ ቀጠና ውስጥ የምትገኝና ምርጥ ተብላ የምትታወቀው (Kepler-186f) የተባለችው ፕላኔት፣ ከዚችኛዋ ጋር ሲነፃፀር በአራት እጥፍ የራቀችና የብርሃን መጠኗም በ20 እጥፍ የደበዘዘ ነው።

ዶክተር ሁዋንግ እንደገለጹት፣ ቡድኑ ግኝቱን መጀመሪያ ሲያይ “ይህ በፍጹም እውነት ሊሆን አይችልም” የሚል እምነት ነበራቸው። “ነገር ግን ሁሉንም ነገር ደጋግመን መረመርን፤ ውጤቱም በንድፈ-ሐሳብ እንደሚገለጸው ትክክለኛ የፕላኔት መጋረድ (transit) ሆኖ አገኘነው” ብለዋል።
ተጨማሪ ምርምርና ስጋቶች
የስዊንበርን ዩኒቨርሲቲ የሰማይ አካላት ተመራማሪ (Astrophysicist) ዶክተር ሳራ ዌብ፣ በጥናቱ ላይ ባይሳተፉም ግኝቱ በጣም አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ፕላኔቷ ‘ሱፐር ስኖውቦል’ (ግዙፍ የበረዶ ኳስ) ልትሆን የምትችልበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል።
ይህም ማለት ከፍተኛ የውኃ መጠን ሊኖራት ቢችልም፣ አብዛኛው ክፍል በበረዶ የተሸፈነ ሊሆን ይችላል። ፕላኔቷን እንደ “Exoplanet” (ከሥርዓተ-ፀሐይ ውጪ ያለች ፕላኔት) ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ዘ ጋርዲያን በድረ-ገጹ አስነብቧል።
በቶለሳ መብራቴ