ጥር 22/2018 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሚያሰራጫቸዉ የይዘት ሥራዎችና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያስመዘገበ ያለዉን ስኬት አጠናክረዉ እንደሚያስቀጥሉ የተቋሙ አመራሮች እና ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2018 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማዉን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋና ሌሎች አመራሮች እና ሰራተኞች በተገኙበት አካሄዷል፡፡
ተሳታፊዎቹ በቀረበዉ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፓርት ላይ በሰጡት አስተያየት ኤኤምኤን በቴሌቭዥን፤ በሬድዮ፤ በዲጂታል ሚዲያ፤ በጋዜጣ፤ በቴክኖሎጂ እና በሰዉ ሃብት ልማት ዘርፎች አመርቂ ዉጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡

ኤ ኤም ኤን በሃገር ዉስጥና በዉጭ ቋንቋዎች እና በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በሚያስተላልፋቸዉ መረጃዎችና የመዝናኛ ዝግጅቶች ተወዳዳሪ የከተማ ሚዲያ እየሆነ መምጣቱን ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡
በርካታ የመንግስትና የግል ተቋማት ከኤ ኤም ኤን ጋር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸዉ፤ ገቢ የማመንጨት አቅሙ ማደጉ፤ ዲጂታል ሚዲያን ጨምሮ በሁሉም ፕላትፎርሞችና ሚዲየሞች የተከታይ ቁጥር እያደገ መምጣቱ ለተገኘዉ ዉጤት ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡
ኤ ኤም ኤን የአፍሪካ መዲና በሆነችዉ አዲስ አበባ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ከመዘገብና ልማቱን ከማስተዋወቁም ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ አዲስ የሬድዮ ትራንስሚተር ወደ ስራ በማስገባት፤ ዘመናዊ ስቱዲዮና የፕሮዳክሽን ግብአቶችን በማሟላት ከተማ እና ሃገር አቀፍ ትላልቅ ሁነቶችን በቀጥታ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የተሰጠዉን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

አገልጋዩ፤ ዋርካና ጠረጴዛን የመሳሰሉ ፕሮግራሞች ህዝብ በቀጥታ የሚናገርባቸዉና የመልካም አስተዳድር ችግሮች የሚቀረፉበት መድረኮች ከመሆናቸዉ በላይ አዲስ ታለንት ሾዉን የመሰሉ የመዝናኛ ፕሮግራሞች በርካታ ህዝብ የሚከታተላቸዉፕሮግራሞች በመሆናቸዉ የተጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ኤ ኤም ኤን ምቹ የስራ አካባቢን ለመፍጠር፤ የሰዉ ሃይልን ለማብቃት፤ ዲጂታል አገልግሎትን ለማስፋፋት፤ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እያደረገ ያለዉ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ ሃገራዊ የምክክር ሂደቱና 7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ አሳታፊ፤ ፍትሃዊና ዴሞክራዊያዊ በሆነ መንገድ እንዲከናዉኑ ሙያዊ ሃላፊነታቸዉን እንደሚወጡም አመራሮቹና ሰራተኞቹ ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ