ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ማጠቃለያ – ክፍል 1

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ማጠቃለያ – ክፍል 1

 ኢኮኖሚ ጉዳዮችን በሚመለከት

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም ከያዛቸው ዋነኛ ዓላማዎች መካከል አንደኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ማረጋጋት ነው። ሁለተኛው የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን ከግብርና መር ወደ ብዝሃ ዘርፍና ብዝሃ ተዋናይ በማሸጋገር ጥራት ያላው እድገት ማስመዝገብ ሲሆን ሌላኛው የኢትዮጵያን የእዳ ጫና ማቃለል ነው። በዚህ ረገድ በሁሉም መመዘኛ በኢትዮጵያ አመርቂ የኢኮኖሚ ስኬት ተመዝግቧል።

 ወጣቶችን ለነገ ውድድር የማዘጋጀት ስራ

ወጣቶችን ለነገ ውድድር ከወዲሁ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ከኢትዮጵያ አምስቱ የእደገት ምሶሶዎች አንደኛው ቴክኖሎጂ እንዲሆን በማደርግ ለትውልድ ሲሰራ ቆይቷል። ኤአይ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛ የሆነውን የኤአይ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት እየተሰራ ነው። ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት አንድ ዓመት ውስጥ ስራ ይጀምራል። ይህ ዩኒቨርሲቲ አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገንብተው ስመጥር እንዳደረጉት ሁሉ ለልጆቻችን ለነገ የተሻለ ዘመን ይዞ ይመጣል።

 ነገን መገንባት

በቴክኖሎጂ ፣ በህጻናት ትምህርት፣ ከተማ ልማት እና አረንጓዴ አሻራ የሰራናቸው ስራዎች የእኛ መንግስት የትናንትና እዳ ለመቀነስ እና ዛሬን እድገት ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን ልጆቻችን ነገ ቀና ብለው ከስደት ተቆጥበው በሀገራችን ሀብት ማፍራት እንዲችሉ በእውቅት እየተመራ መሆኑን ያሳያል።

 የእድገት ትንበያ

ኢትዮጵያ ነዳጅ ሳይኖራቸው ቀዳሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በዘንድሮው በጀት ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት የእድገት አፈጻጸም በመገምገም ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ የ10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንድምታስመዘግብ የእቅድ ማሻሻያ ተደርጓል። ይህ ትንበያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ጋር የተቀራረበ ነው።

 የዘርፍች እድገት አፈጻጸም- ግብርና

ባለፉት ስድስት ወራት 999 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ይህም ከዓመቱ እቅዳችን 78 በመቶ የሚሸፍን ነው። በተለይ በሰብል በሆረቲ ካልቸርና በጥጥ ከእቅድ አንጻር 79 በመቶ ማሳካት ተችሏል። በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ይህን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ከእቅድ በላይ ማሳካት ይቻላል።

 የግብርና ግብዓቶች ተደራሽነት

•⁠ ⁠በ2010 ዓም በኢትዮጵያ 4 ሺህ 700 ትርክተር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ይህ አሃዝ ወደ 27 ሺህ 200 አድጓል።

•⁠ ⁠በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ 338 ኮምባይነር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ይህ አሃዝ ወደ 8 ሺህ 700 አድጓል

•⁠ ⁠በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ 6 ሺህ የመስኖ ውሃ ፓምፖች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ይህ አሃዝ ወደ 280 ሺህ አድጓል

 የዘርፎች አፈጻጸም- ኢንዱስትሪ

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር የኢትዮጵያ ኢንዱስትርዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ አይበልጥም ነበር ይህን አሁን በሶስት ዓመት ብቻ 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀም 16 በመቶ አድጓል። በንቅናቄው አማካኝነትም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶለር ያወጡ የነበሩ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል። ከኢንዱስትሪ የሚገኘው የወጪ ንግድም የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

 የዘርፎች አፈጻጸም -ማዕድን

የማዕድን ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት የ30 በመቶ የገቢ ጭማሪ አሳይቷል። የብረት ምርት 36 በመቶ እንዲሁም ሲምንቶ ምርት 28 በመቶ ጨምሯል። ይህም በተለይ የቤት ልማት እየተስፋፋ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ነው።

 የዘርፎች አፈጻጸም – አገልግሎት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በለውጡ ጅማሬ በዓመት ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞችን ያጓጉዝ ነበር። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎችን አጓጉዟል። የሞባይል ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥርም በለውጡ ጅማሬ 37 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ይህ አሃዝ አሁን ላይ 97 ሚሊዮን ደርሷል። የ5 ጂ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥርም በቅርቡ 30 የሚደርስ ይሆናል። የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥርም 58 ሚሊዮን ደርሷል። ይህም የፖሊሲ ትኩረት ውጤት ነው።

 የገቢ እድገት

የበጀት ዓመቱ ሲጀመር መንግስት 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ የያዘ ሲሆን፤ ባለፉስ ስድስት ወራት ብቻ 709 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል። ይህም ትልቅ አፈጻጸም ቢሆንም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ግን አሁንም ብዙ መስራት እንዳለብን ያሳያል። ከወጪ አንጻርም መንግስት በስድስት ወራቱ ለማውጣት ካቀደው ገንዘብ 48 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ ወጪ አድርጓል።

 እዳ ቅነሳ

ይህ መንግስት አንዱ ክብር የሚያሰጠው ስራ እዳ ላይ የሰራው ስራ ነው። በለውጡ ጅማሪ ኢትዮጵያ በከፍተኛ እዳ ውስጥ የነበረች ሀገር ናት። ከለውጡ በኋላ ይህ መንግስት አንድ ዶላር የንግድ ብድር ስምምነት አላደርገም። ይህ ከፍተኛ ምስጋና የሚገባው ጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው። የንግድ ብድር ያበደሩን ወዳጆቻችን “ብድሩ ተገቢ አይደለምና ወደ ትክክለኛው የብድር ስርዓት መመለስ አለበት” በሚል ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ከፍትኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። ከሞላ ጎደል ይህ ጥረት ተሳክቶልናል።

 ህዳሴ ግድብ- በኢትዮጵያዊያን ሃብት ብቻ የተገነባ ታላቅ ፕሮጀክት

የህዳሴ ግድብን ያለ አንድ ብር እርዳታና ብድር ያሳካ መንግስት ፕሮጀክት አይሰራም ሊባል አይችልም። በህዳሴ ላይ አንድ ብር እርዳታ ብድር ኢትዮጵያ አልወሰደችም፤ በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ቁርጠኛ አቋም ጨክነው በጋራ ቁመው ስለሰሩ የተከወነ የጋራ ፕሮጀክት ነው።

 የፕሮጀክት አመራር

በሚጋ ፕሮጀክት ክትትል፣ አፈጻጸምና አመራር ላይ ድፍን አፍሪካ ከኢትዮጵያ ይማራል። በሳምንት ሰባት ቀንና ማታ በየጥሻው የምንቀሳቀሰው ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንዳይቆሙ ነው።

 የወጪ ንግድ አፈጻጸም

ባለፉት ስድስት ወራት ከሸቀጦች ወጪ ንግድ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። ይህም ከእቅዱ አንጻር የ120 በመቶ አፈጻጸም ያሳያል። ከአገልግሎት ወጪ ንግድም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሆም ከሃዋላ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በስድስት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብም የተሳካ የማክሮ ኢኮኖሚ ስራ ተከናውኗል።

 የዋጋ ንረትን ማረጋጋት

በብዙ ጥረትና ስራ በዘንድሮው ዓመት የዋጋ ንረቱን ወደ አንድ አሃዝ ማውረድ ተችሏል። በዘንድሮው ዓመት የዋጋ ንረቱ ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ወርዷል። ይህም ሆኖ ዋና ዋና ጉዳዮችን በመለየት የኑሮ ጫናውን ለማቃለል እየተሰራ ነው። በዚህም የምግብ ተደራሽነት ማስፋት፣ የቤት ተደራሽነትን ማሻሻል እንዲሁም የትራንስፖርት አማራጭን ማስፋት ላይ እየተሰራ ነው። በተለይ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በዝቅተኛ ዋጋ የሚሰሩና በጋዝ የሚንቀሳቀሱ አውቶብሶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው። የትምህርት ቤት ምገባም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review