AMN ጥር 26/2018
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የጋራ አጀንዳ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቀይ ባሕርን ጉዳይ በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያለው ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ለዘለዓለም ተነጣጥለው እንደማይኖሩ በመግለጽ ፍትሐዊ ጥያቄያችን በሰላማዊ፣ በሰጥቶ መቀበልና በድርድር መርህ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ፍትሐዊ ካልሆነ በዓለም ላይ ፍትሕ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መልስ ማግኘቱ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ምንም አይነት ልዩነት ሳይገድበን የጋራ አቋም ሊኖረን ይገባል ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅም የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ የባህር በር ጉዳይን በሰላማዊ መንገድ ዕልባት እንዲያገኝ ማድረግ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡