በህገወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ ከተሳተፉ አካላት 200 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ነዳጅ ተወርሷል

You are currently viewing በህገወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ ከተሳተፉ አካላት 200 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ነዳጅ ተወርሷል

AMN ጥር 26/2018 ዓ.ም

በነዳጅ ግብይት ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳሰበ።

ህጋዊ የነዳጅ ግብይትን ለማሳለጥ ያለመ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአዳማ ገልመ አባገዳ ተካገሂዷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የነዳጅ ግብይትን ለማሳለጥና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

መንግሰት ከፍተኛ ገንዘብ በመበጀት ነዳጅ ከውጭ በማስገባት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ እያደረገ ቢሆንም በነዳጅ ግብይት ላይ ተግዳሮቶችና ክፍተቶች አሉ ብለዋል።

በተለይ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም ቅሸባና በወቅቱ ያለማጓጓዝ ችግር እንዲሁም በነዳጅ ማደያዎች የሚታይ የግብይት ችግሮች ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ዲጂታል የነዳጅ ግብይት አሰራር ከመዘርጋትም ባለፈ ብሔራዊ የነዳጅ ግብይት መቆጣጠሪያ ስርዓት ስራ ላይ በመዋሉ ውጤታማ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።

በህገወጥ ተግባር ውስጥ የገቡ አካላት ተጠያቂ እየሆኑ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም 200 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ነዳጅ መወረሱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይም በህገወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የተሳተፉ 62 ግለሰቦች መቀጣታቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ 354 ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስረድተዋል።

በነዳጅ ግብይት ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ነዳጅን መደበቅና ተጠቃሚዎችን ማጉላላት፣ ከገበያ መዳረሻ ውጭ ይዞ መጓዝና በህገወጥ መንገድ መሸጥ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ችግሩን ለማስወገድም ህጋዊ አሰራርና የዋጋ መመሪያዎችን ተፈፃሚ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው በነዳጅ ግብይት የሚሳተፉ ኩባንያዎች፣ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎችና ማደያዎች በተቀናጀ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።

የዛሬው መድረክም በነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በቅንጅት ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለዉ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review