አዲስ አበባ በገቢ አሰባሰብና በጀትን ለዘላቂ ልማት በማዋል ከአፍሪካ 6 ከተሞች ቀዳሚ ሆናለች – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አበባ በገቢ አሰባሰብና በጀትን ለዘላቂ ልማት በማዋል ከአፍሪካ 6 ከተሞች ቀዳሚ ሆናለች – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN — ጥር 29/ 2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያከናወነ በሚገኝበት ጉባዔ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ከንቲባዋ እንደገለጹት ባለፉት 6 ወራት 162.72 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 92.4 በመቶ አሳክቷል። ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ45.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም የአዲስ አበባ ከተማ በጀትን ለዘላቂ ልማት በማዋል ረገድ ከአፍሪካ 6 ከተሞች ጋር በተደረገ ምዘና ቀዳሚ መሆኗን በሪፖርታቸው ገልጸዋል። ከጠቅላላ በጀቱ 71.9 በመቶ ወይም 251.64 ቢሊዮን ብር ለዕድገት ተኮር ዘላቂ ልማት መመደቡንም አንስተዋል፡፡

በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ሥራ በመሥራት ደረሰኝ ሳይቆርጡ በተገኙ 7,678 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ ብልሹ አሠራር በፈጸሙ 282 ሠራተኞች ላይም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱንም በሪፖርታቸው ተናግረዋል።

የኑሮ ጫናን ለመቀነስ 18.72 ቢሊዮን ብር ለተማሪ ምገባ፣ ለዩኒፎርም፣ ለጤና መድህንና ለትራንስፖርት ድጎማ መዋሉን ገልጸው በልማታዊ ሴፍቲኔት ደግሞ 1.135 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

በ58 ተቋማት ላይ የ164.5 ሚሊዮን ብር የኦዲት ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን፤ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ (e-GP) ሥርዓትን የሚተገብሩ ተጨማሪ 48 ተቋማት ወደ ሥርዓቱ መግባታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review