የቀጠለው የአንድ ጀንበር ፍካት

You are currently viewing የቀጠለው የአንድ ጀንበር ፍካት

• በአንድ ጀንበር ለ3 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የሚያስገኘው የሥራ ዕድል ፈጠራ አውደ ርዕይ መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል  

አዲስ አበባ ትኩረት ሰጥታ እያከናወነቻቸው ካሉ ተግባራት መካከል የስራ ዕድል ፈጠራ አንዱ ነው፡፡ ለዚህም የስራ ዕድል መፍጠሪያ አቅሟችን በማማተርና ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ተስፋ ሰጪ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የአንድ ጀንበር የስራ ዕድል ፈጠራን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡ 

የዚህ አካል የሆነው እና በአንድ ቀን ውስጥ 3 ሺህ ለሚሆኑ ሥራ ፈላጊ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የሚፈጥር የሥራ ዕድል ፈጠራ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተሰናዳ እንደሆነ ከሥራና ክህሎት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቢሮው የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ መጋቢት 02 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው ከተማ አቀፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ አውደ ርዕይ መርሃ ግብር ቁጥራቸው 11 ሺህ የሚደርሱ ሥራ ፈላጊ የኮሌጅ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንን በቋሚ የሥራ ዕድል የማስቀጠር ዓላማ የያዘ ነው። ከሥራ ፈላጊዎቹ መካከል ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት መርሃ ግብሩ በሚካሄድበት ዕለት ቋሚ የሥራ ዕድል የሚያገኙ ይሆናል፡፡

ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፣ በአውደ ርዕዩ ለሥራ ፈላጊዎቹ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ 200 የሚደርሱ የግል ድርጅቶች ይሳተፋሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በአምስቱ ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ማለትም፡- በአምራች (ማኑፋክቸሪንግ)፣ በግንባታ (ኮንስትራክሽን)፣ በአገልግሎት፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድ እና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ዲጂታል ሲስተም) የተሰማሩ ናቸው ብለዋል፡፡

አክለው እንዳስረዱት፤ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በአውደ ርዕዩ ላይ የሚሳተፉ ከ10 እስከ 1 ሺህ ቋሚ ሠራተኞችን የመቅጠር አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ በዕለቱ ቋሚ የሥራ ዕድል ከሚፈጠርላቸው 3 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች ውጪ ያሉ ቀሪ ሥራ ፈላጊዎች ከድርጅቶቹ ጋር በሚፈጠር ውል መሠረት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ የሚመቻች ይሆናል፡፡

የሥራ ፈጠራ አውደ ርዕይ መርሃ ግብሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የሚከናወን መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰብሃዲን፤ ሥራውን በስኬታማነት ለማጠናቀቅ የተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት በጋራ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው። ተግባራትን በቅንጅት በማከናወኑ ሂደት ላይ ከሚሳተፉ ተቋማት መካከል፦ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ቱሪዝም ኮሚሽን፣ የተለያዩ አንቀሳቃሾች (ኢንተርፕራይዞች) እንዲሁም የኦንላይን ሥራዎችን የሚሠሩ ተቋማት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

በአንድ ቀን ሺዎችን የሥራ ባለቤት ማድረግ የሚያስችል መርሃ ግብር የማዘጋጀት ልምዱ እየዳበረ መምጣቱን ያነሱት አቶ ሰብሃዲን፤ ክፍለ ከተሞች በራሳቸው መሰል የሥራ ዕድል ፈጠራ አውደ ርዕይ ማሰናዳታቸውን በማስታወስ፤ በዚህም እያንዳንዳቸው 1 ሺህ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሥራ ፈላጊዎችን ወደ ሥራ አስገብተዋል፡፡ መርሃ ግብሩ በከተማ አስተዳደር ደረጃ በየሦስት ወሩ በዕቅድ ተይዞ ተፈፃሚ እየሆነ እንደሚገኝ እንዲሁም መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚካሄደው በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ከተያዙት መካከል ሦስተኛው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የሥራ ዕድል ፈጠራ አውደ ርዕዮች በእያንዳንዳቸው ከ100 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰዋል፡፡

አቶ ሰብሃዲን በሰጡን መረጃ መሰረት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አማካኝነት በ2018 በጀት ዓመት ለ350 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ 257 ሺህ 67 የሥራ ዕድል በስምንት ወራት ውስጥ ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፤ ለ287 ሺህ 652 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል። ይህም ከዕቅዱ አንፃር የ111 ከመቶ አፈፃፀም እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡ ከተፈጠረው ቋሚ የሥራ ዕድል ውስጥ 14 ሺህ 51 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገበት ተግባር የሚጠቀስ ነው፡፡ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች በውስጣቸው 82 ሺህ 14 አንቀሳቃሾችን ይዘዋል፡፡

እንደ ከተማ አስተዳደር የተያዘውን ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት (በወርሃ መጋቢት መጨረሻ ላይ) ለማሳካት እየተሠራ ሲሆን፤ እስካሁን ያለው አፈፃፀምም ይህንን ለማሳካት እንደሚቻል ጠቋሚ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራን ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ አንፃር የአፈፃፀም ውጤቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ያነሱት አቶ ሰብሃዲን፤ የስኬታማነት ምክንያቱንም አንስተዋል። እንደሳቸው ገለፃ፤ “ለስኬታማነቱ አጋዥ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል፡- የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ‘የሥራ ዕድል ፈጠራን ቁልፍ የትኩረት መስክ’ ማድረጋቸውና ለዚህም ስኬት ያለመታከት የመሪነት ሚና መወጣታቸው፤ በበጀት ዓመቱ ሦስት ትላልቅ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ የንቅናቄ መድረኮችን ለማዘጋጀት ዕቅድ መቀመጡ እና በውጤታማነት መፈፀሙ፤ ፀጋዎችን በጥናት በመለየት፣ የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር ውይይት በማድረግ፣ የሥራ ፈላጊዎችን ስለሥራ ያላቸውን አመለካከት የሚያሻሽል ስልጠና በመስጠት፣ ወደ ሥራ እንዲገቡ በጋራ እና በቅንጅት የመንቀሳቀሱ ልምድ እየዳበረ መምጣቱ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ የሥራ ባህልን ለማሻሻል የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እንደተቋም በተለያዩ አደረጃጀቶች አማካኝነት ወደ ሕብረተሰቡ እየደረሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም በ4 ሺህ 210 የብሎክ አደረጃጀቶች እየተጠቀመበት ያለው አሠራር ማሳያ ነው”፡፡

በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት፤ “የሥራ ዕድል ፈጠራ ዓውደ ርዕይ ላይ በመሳተፍ የቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊውን ስልጠና የወሰዱ፣ የተመረጡና ለሥራ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶች በዕለቱ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በየጊዜው ለውጥ እየታየበት ቢሆንም የሥራ ማማረጥ አጉል ልምድን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ሥራ የለም የሚልን አስተሳሰብ በመተው መንግስት በሚያመቻቸው የሥራ መፍጠሪያ የሥራ ዕድሎች መጠቀም ይገባል፡፡” ብለዋል፡፡

በደረጃ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review