AMN- የካቲት 6/2018 ዓ.ም
ችግኝ መትከል የመጀመሪያው እርምጃ ቢሆንም፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ለምለም አካባቢ ለመፍጠር ግን እንክብካቤ ወሳኝና የማይተካ ሚና እንዳለው በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከሏቸውን ችግኞች በዛሬው ዕለት የመንከባከብ ስራ አከናውነዋል።
ይህ ተግባር ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን፣ የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለውጤት እንዲበቁ ተከታታይነት ያለው ክትትል ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ለማሳየት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ችግኝ መትከል ተስፋ ሲሆን መንከባከብ ደግሞ ያንን ተስፋ ማጽናት ነው። ለምለም አካባቢ ሊፈጠር የሚችለውም ችግኞቹ በየጊዜው ውሃ ሲጠጡና ክትትል ሲደረግላቸው ብቻ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያደጁ አሳስበዋል።
ኢንጂነር ወንድሙ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የመንግስት ተቋማት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ገልጸው፣ የተራቆተ መሬት አገግሞ የነገ ተስፋ እንዲሆንና የከተማዋን የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ እንክብካቤው ወሳኝ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
በእንክብካቤ ሥራው ላይ የተሳተፉ ሰራተኞች በበኩላቸው፤ ችግኞችን መንከባከብ ልጆችን እንደማሳደግ ትዕግስትና ፍቅር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። ዛሬ የሚደረገው እንክብካቤ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ለምለም አካባቢ ለመፍጠር ዋስትና መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቶለሳ መብራቴ