AMN- የካቲት 10/2018 ዓ.ም
ቻይናዊያን አዲሱን ዓመት 2026 በተለያዩ ዝግጅቶችና ፌስቲቫሎች በመቀበል ላይ ይገኛሉ፡፡
ለ15 ቀናት ያህል በተከታታይ የሚከበረዉ ይህ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል እንደ ቻይናዊያኑ የከዋክብት ቆጣሪዎች “የእሳት ፈረስ“ ተብሎ ይጠራል፡፡
በዓሉ በክረምት ወቅት ላይ የሚከበር ቢሆንም “የፀደይ በዓል” ተብሎ ይጠራል፤ ምክንያቱ ደግሞ የበረዶው ወቅት ማብቂያ እና የጨረቃ አቆጣጠር የፀደይ መጀመሪያን ስለሚያመለክት ነዉ፡፡
በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናዊያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ወደ ትውልድ ቀዬቸው የሚጓዙበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በዓሉ “ቹኑን” በዓለም ላይ ግዙፉ የሰው ልጆች ፍልሰት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ቻይናዊያን አዲስ ዓመት በሚከበርበት ዕለት መጥረጊያ አይነኩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የገባውን መልካም ዕድል በስህተት “ጠርገው ሊያወጡት” ይችላሉ የሚል እምነት ስላላቸዉ ነዉ፡፡
ጸጉርን መቁረጥ “ሀብትን የመቁረጥ” ያህል ይታያል፤ በአዲስ ዓመት ቀን ካለቀሱ ዓመቱን ሙሉ ሲያለቅሱ ይኖራሉ ተብሎም ይታመናል። በዚህ የተነሳ ወላጆች ለልጆቻቸው ልዩ ትዕግስትን ያሳያሉ፡፡
ቻይናዊያኑ አዲሱን ዓመት በሚያከብሩበት ወቅት ቀይ ቀለም ያላቸዉ ልብሶችንና ጌጣጌጦችን በብዛት ይጠቀማሉ፡፡ ጫጫታም የተለመደ ነዉ፡፡
ይህ ባህል “ኒያን” ከሚባለው አስፈሪ አውሬ አፈ ታሪክ የመጣ መሆኑን የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ይህ አውሬ በየአዲሱ ዓመት እንስሳትንና መንደርተኞችን ለመብላት ይመጣ ነበር። ሰዎች ግን ኒያን ቀይ ቀለምን፣ ብሩህ ብርሃንንና ከፍተኛ ጫጫታን እንደሚፈራ ደረሱበት። ለዚህም ነው ቤቶች በቀይ ጌጣጌጦች የሚሸለሙት፤ በእኩለ ሌሊት ርችቶችን የሚተኮሱት።
በወንድማገኝ አሰፋ