ከጋና እስከ ኬኒያ- ፓርላማዎችን ያነጋገረው የአዲስ አበባ የማያቋርጥ ለውጥ

You are currently viewing ከጋና እስከ ኬኒያ- ፓርላማዎችን ያነጋገረው የአዲስ አበባ የማያቋርጥ ለውጥ

AMN- የካቲት 12/2018 ዓ.ም

3ኛዋ የዓለም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል፤ የፓን አፍሪካ ትርክት እምብርት፤ የአሕጉሪቱ ፖለቲካ አስኳል እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ በመሆኗ በበርካቶች እየተጎበኘች ትገኛለች አዲስ አበባ ከተማ።

በቅርቡ የጋና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሃጂያ ዙወራ መሐመድ በሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ ቆይተው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ፤ ለጋና ፓርላማ አባላት ስለ አዲስ አበባ የተናገሩት በተለያዩ መገናኛ ብዙኋን በስፋት ተዘግቧል፡፡

“በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ሄጄ ካረፍኩበት ሆቴል ወደ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በመኪና እየተጓዝኩ፣ አዲስ አበባ ከተማ አስደማሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን ማየት ችያለሁ” ብለዋል ሃጂያ ዙወራ መሐመድ።

“በጉዟችን ወቅት አዲስ አበባ እያስመዘገበችው ስለላው አስደማሚ ዕድገት ብቻ ነበር ስናወራ የነበረው” በማለት ነው ለፓርላማው የአዲስ አበባን ዕድገት የገለጹት።

የአዲስ አበባ ዕድገት እና ለውጥ “እኛ ጋናውያን በሀገራችን ምን ሰራን? ይህን መሰል ልማት በአዲስ አበባ እንዴት ሊሰካ ቻለ?” ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደረገ ነውም ብለዋል።

“ከ5 ዓመታት በፊት የማውቃትን አዲስ አበባ ከተማ ከሰሞኑ ሄጄ ስመለከታት መለየት እስኪቸግረኝ ተለውጣ፣ እጅግ ዘመናዊ ሕንፃዎች ተገንብተው፣ ባለ 4 እና 5 መስመር ያላቸው የመኪና መንገዶች ተሰርተው አይቻለሁም” ነው ያሉት።

ከሰሞኑ ደግሞ የኬንያ ፓርላማ አባል ጁኔት መሐመድ እና ሌላ የፓርላማ አባል፣ አዲስ አበባ ከተማ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን እድገት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአዲሷ አፍሪካ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን ላይ አዲስ አበባ የአፍሪካዋ ዱባይ ናት ያሉት የፓርላማ አባላቱ፣ ወደ ዘመናዊ ከተማነት እንዴት እንደቀየሯት ከሀገሪቱ ብዙ የምንማረው ትምህርት አለ ሲሉም ገልጸዋል።

የከተማዋ እድገት በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አዎንታዊ መሆኑና ማህበረሰቡን ይበልጥ እንደሚያቀራርብም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ 130 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሀገር መሆኗን በመጥቀስም፣ ለኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የገቢና ወጪ ንግድ አማራጭ በመሆን የሚያገለግለው የላሙ ወደብ ሊሰጣት ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ በመሆኗ እና በኬንያ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ውድ በመሆኑ ከሀገሪቱ ብዙ ኃይል ማስገባት አለብን ብለዋል።

የፓርላማ አባሉ አክለውም፤ በአዲስ አበባ ከተማ የታየው የጥራትና የፍጥነት ለውጥ ወደ እውነተኛ ለውጥ ለመሻገር የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራት እርስ በእርስ በመማማር የቀጣናውን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review