ተመራጭ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ራዕይን ሰንቃ በመትጋት ላይ የምትገኘዉ አዲስ አበባ

You are currently viewing ተመራጭ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ራዕይን ሰንቃ በመትጋት ላይ የምትገኘዉ አዲስ አበባ

AMN- የካቲት 14/2018 ዓ.ም

በዓለም ላይ በርካታ ግለሰቦች የተሻለ ህክምና ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ አዉጥተዉ ባህር አቋርጠዉ ይጓዛሉ፡፡

ከአሁን ቀድም በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ታካሚዎች የተሻለ ህክምና ለማግኘት አሜሪካና ብሪታንያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ምዕራባዊያን ሀገራት ሲጓዙ የነበረ ቢሆንም ሕንድ፣ ታይላንድ እና ቱርክን በመሳሰሉ ሃገራት የተሻለ ህክምናን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

በሰለጠነዉ ዓለም የህክምና ቱሪዝም ተብሎ የሚጠራዉ ይህ ዘርፈ ብዙ የህክምና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ፤ በተሻለ ጥበቃ፤ በታወቁ የህክምና ባለሙያዎች፤ አስተማማኝ ህክምናና የማገገም አገልግሎት ማግኘትን ያካትታል፡፡

ይህንን እና መሰል አገልግሎቶችን የሚሰጡት የጤና ተቋማት ደግሞ እዉቅና የተሰጣቸዉ እና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሆስፒታሎች ናቸዉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የአፍሪካ መዲናና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መገኛ በሆነችዉ አዲስ አበባ ይህንን የህክምና ቱሪዝም ተግባራዊ ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

መስተዳድሩ የተያዘዉን ራዕይ ዕዉን ለማድረግ አዳዲስ የጤና ተቋማትን በመገንባት፤ ለነባሮቹ የማስፋፊያ ስራዎችን በማከናወን፣ የህክምና ግብአቶችን በማሟላት፡ ዘርፉ የሚፈልገዉን የሰዉ ሃይል በማብቃት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ ዉጤታማ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የጤና ተቋማትን ፍትሃዊ ተደራሽነት ከማሳደግ ረገድም በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 9 አዲስ ጤና ጣቢያዎች ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን 13 ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ሰፊ የማስፋፊያ ግንባታ ተከናውኖላቸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ነባሩን የሆስፒታል አቅም ከእጥፍ በላይ በሚያሳድግ የላቀ ህክምና ማእከል በመገንባትና በዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች በማደራጀት ህብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል፡፡

የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል እና የዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታልም ግዙፍ የማስፋፊያ ግንባታ ተደርጎላቸዋል፡፡

ሆስፒታሎቹ በዘመናዊ ህክምና ግብአቶች ተደራጅተዉ ለአገልግሎት ዝግጁ እየተደረጉ የሚገኙ ሲሆን፣ ሁሉም ሆስፒታሎች የራሳቸው የኦክስጅን ማምረቻና ዘመናዊ የኦክስጅን አገልግሎት መስጫ አሰራር እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጤና መሰረተ ልማትና አገልግሎትን ከማሻሻል አንፃር በበጀት አመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት የከተማ አስተዳደሩ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የያዘዉን ራዕይ እዉን ለማድረግ የሶስት ግዙፍ እና ዘመናዊ ሆስፒታሎች ግንባታ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ5 መቶ አልጋዎች በላይ የሚኖራቸው የኮልፌ መንዲዳ እና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ሁለት ግዙፍ ዘመናዊ ሆስፒታሎች እንዲሁም በሀገሪቱ በአይነቱ የመጀመሪያ እና ልዩ የሆነው ከ511 በላይ አልጋዎች የሚኖሩት የገላን ትራውማ ሆስፒታልን (Gelan Trauma Hospital) ጨምሮ በአጠቃላይ ሶስት አዲስ ሆስፒታሎች ግንባታቸው ተጠናቀው የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከተጀመሩ ዉጤታማ ስራዎች በተጨማሪ የግል ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዘርፉ የሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ መዲናዋን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘዉን ራዕይ ለማሳከት የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review