AMN – የካቲት 15/2018ዓ.ም
በአዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ማነቆዎች የተቀረፉላቸው ኢንደስትሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በንቅናቄው ከማምረት ውጭ ሆነው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንዱስትሪዎች ችግራቸውን በመለየት እና መፍትሔ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ልዩ እገዛ መደረጉን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል፡፡
ከንቲባዋ ከኤ.ኤም.ኤን ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የማምረቻ ቦታ በማቅረብ፣ ማስፋፊያ መሬት በማዘጋጀት፣ የመንገድ መሠረተ ልማት በማሟላት፣ ኃይል በበቂ መጠን እንዲያገኙ፣ የካፒታል ብድር በማመቻቸት ኢንዱስትዎቹን የማነቃቃትና የመደገፍ ስራ መከናዎኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ድጋፍ የተደረገላቸው ኢንዱስትሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ከንቲባዋ ጠቅሰዋል፡፡
በኢንዱስትሪዎች የስራ ዕድል ያገኙትም በንቅናቄው ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በስደት መቆየቱን የሚናገረው ቅዱስ ተባረክ ወደ ሐገር ተመልሶ ባገኘው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆኑንና ወደ ስደት የሄደበትን መንገድ መለስ ብሎ እንደሚቆጭ ገልጿል፡፡
ወጣቱ ሀገሩ ላይ ሆኖ ከትንሽዬ ተነስቶ ትልቅ ነገር ላይ መድረስ እንደሚቻል እኔ አይቼዋለሁ ሲልም ተሞክሮውን አጋርቷል፡፡
በዱቄት ፋብሪካ ውስጥ የምትሰራው መስከረም ቶለሳ የተፈጠረላት የስራ ዕድል ቤተሰቧን ማስተዳደር እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ኢንደስትሪዎች በርካታ የሰለጠኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ እያካተቱ መሆናቸውን የጠቀሱት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዐባይ፣ በተለይ ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ገልጸዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ምዝገባ ውስጥ የተካተቱ ወጣት ሴቶች ወደ 30 ሺህ እንደሚደርሱና ዲጂታል ምዘገባው ያላለቀ በመሆኑ እንጂ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው