AMN- የካቲት 16/2018 ዓ.ም
የጀርባ ሕመም በዓለማችን ላይ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃና ለሥራ መስተጓጎል ዋነኛ ምክንያት እየሆነ የመጣ የጤና ችግር ነው።
አብዛኛው የጀርባ ሕመም ከባድ ባልሆኑ ምክንያቶች የሚከሰት ቢሆንም፣ የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከልና ተገቢውን ሕክምና በማግኘት መከላከልና መፈወስ እንደሚቻል በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ናታን ወንድወሰን ከኢ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።
ዶ/ር ናታን እንደገለጹት፤ የጀርባ ሕመም በተለያዩ መንስኤዎች ሊከሰት የሚችል ሲሆን፣ ዋነኞቹ መነሻዎች የጡንቻ መሸማቀቅ ወይም ድንገተኛ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ጊዜ የሚከሰት የጡንቻ መሳብ ናቸው።

ሕመሙ በአከርካሪ አጥንት መካከል ያሉ ዲስኮች በመንሸራተት በነርቮች ላይ ጫና በሚፈጥሩበት ጊዜም ሊከሰት ይችላል።
ሌላውና በብዛት የሚስተዋለው መንስኤ የአቀማመጥ ስህተት ሲሆን፣ በተለይም ለረጅም ሰዓት ጎብጦ መቀመጥ ወይም መቆም በጀርባ አጥንትና ጡንቻዎች ላይ ከፍተኛ ጫናን በመፍጠር ለሕመሙ ያጋልጣል ሲሉ ዶ/ር ናታን አስረድተዋል።
በተጨማሪ እንደ አጥንት መሳሳት፣ የአርትራይተስ ሕመም እና የኩላሊት ጠጠር ያሉ የጤና ችግሮችም አልፎ አልፎ ለጀርባ ሕመም መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሐኪሙ አብራርተዋል።
ይህንን ችግር ለመከላከል ቀዳሚው መንገድ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ናታን፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር በጀርባ አጥንት ላይ የሚፈጠር ጫናን እንደሚቀንስ ገልጸዋል።
የጀርባና የሆድ ጡንቻዎችን የሚያጠነክሩ እንቅስቃሴዎችን እንደ የእግር ጉዞ እና ዋና ማዘውተር ለአከርካሪ አጥንት ጥንካሬ ወሳኝ በመሆኑ ሕመሙ ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ መከላከል ያስችላል።
በተጨማሪም ስንቀመጥም ሆነ ስንቆም ጀርባን ቀጥ አድርጎ የመያዝ ልምድን ማዳበርና ከባድ ዕቃዎችን ከምድር ላይ ሲያነሱ በጀርባ ከመጎንበስ ይልቅ ጉልበትን በማጠፍ መሆን እንዳለበት መክረዋል።

የጀርባ ሕመም እንደ ደረጃው የተለያዩ የሕክምና አማራጮች ያሉት ሲሆን፣ ለቀላል ሕመም ዕረፍት ማድረግና በበረዶ ወይም በሙቅ ውኃ የታመመውን ቦታ መታሸት እንደ መጀመሪያ ደረጃ መፍትሔ ይወሰዳል።
ሕመሙ ጠንከር ያለ ከሆነ ደግሞ በባለሙያ ታግዞ የሚደረግ የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ወይም በሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ የሕመም ማስታገሻዎችና የጡንቻ መዝናኛ መድኃኒቶች መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሌሎች የሕክምና አማራጮች ውጤት ካላመጡና ችግሩ ከነርቭ መጎዳት ጋር የተያያዘ ከሆነ የቀዶ ሕክምና የመጨረሻው አማራጭ ተደርጎ እንደሚወሰድ ዶ/ር ናታን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ ሕመሙ ከሰሞንኛ ድካም ያለፈ ከሆነ፣ በእግር ላይ የመደንዘዝ ስሜት ካለው ወይም ከከፍተኛ ትኩሳት ጋር ተያይዞ ከመጣ በአስቸኳይ ሐኪም ማነጋገር እንደሚገባ ዶ/ር ናታን ወንድወሰን ከኢ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው