AMN – የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት አራት ዓመታት አመርቂ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ የቀሩትን ወሳኝና መሠረታዊ ተግባራት በአግባቡ ለማጠናቀቅ እንዲቻል፣ ለተጨማሪ ስምንት ወራት ማራዘሙ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ይህንን ተጨማሪ ጊዜ በመጠቀም ሀገራዊ ምክክሩን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ስልታዊ ተግባራትን ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኑን ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል።
በቀጣዮቹ ስምንት ወራት ውስጥ ከሚከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል ዋነኛው በትግራይ ክልል የሚካሄደው የምክክር ሂደት መሆኑም ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ በክልሉ ያለውን የምክክር ሂደት በንቃት በማከናወን፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ መድረክ ለመፍጠር በትኩረት ለመስራት ዝግጅት አድርጓል።
ከዚህ ጎን ለጎን እስካሁን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በማቅረብ፣ በየፈርጃቸው በመለየትና በመቅረጽ አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።
የምክክር ሂደቱ በባለሙያ የታገዘና የተሳካ እንዲሆን ለማድረግም፣ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዝግጁ የሆኑ አወያዮችንና አመቻቾችን የመለየት፣ የማሰልጠንና የማብቃት ተግባራት በስፋት ይከናወናል ብሏል።
ይህ ዝግጅት ኮሚሽኑ ወደፊት ለሚያካሂደው አሳታፊና አካታች ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እንደ ዋነኛ መሠረት የሚያገለግል ነው።
ከጉባኤው በኋላም የሚገኙ ውጤቶችና ምክረ-ሀሳቦች በአግባቡ ተጠናቅረው እንዲዘጋጁና የተግባራዊነታቸው ሂደት በቅርበት ክትትል የሚደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ የምክክሩን ሂደት የቴክኖሎጂ አካል ለማድረግ የሰነድ አያያዝ ስራዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሥርዓት የመቀየርና ተደራሽነቱን የማስፋት እቅድ ተይዟል።
ይህ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚደረገው የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ጋር ተቀናጅቶ የሚከናወን ሲሆን፣ ይህም የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በበረከት ጌታቸው