አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኩራትና የእንግዶች ዓይን ማረፊያ ሆናለች- ኮሎኔል ጌቱ ታዬ

You are currently viewing አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኩራትና የእንግዶች ዓይን ማረፊያ ሆናለች- ኮሎኔል ጌቱ ታዬ

AMN- የካቲት 17/2018 ዓ.ም

በከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው አስገራሚ የኮሪደር ልማትና የከተማ ማሻሻያ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችንና የሰላም ማስከበር ሰልጣኞችን በእጅግ እያስደመመ ይገኛል፡፡

የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም አዛዥ ኮሎኔል ጌቱ ታዬ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ለማዘመን፣ ምቹ እና ሳቢ ለማድረግ የሰራው ስራ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ማሰልጠኛ ተቋሙ የሚመጡ እንግዶችን ማስደመሙን ገልጸዋል።

ኮሎኔል ጌቱ እንደሚሉት፣ በተለይ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባን የሚያውቁ የውጭ ሀገር ዜጎች አሁን ያለውን ለውጥ ሲመለከቱ ከፍተኛ አግራሞት ይፈጥርባቸዋል፡፡

ከእኛ ጋር ከ10 ዓመት በላይ አብረው የሰሩ እንደ ብሪቲሽ ፒስ ሰፖርት ቲም አፍሪካ ያሉ ተማሪዎችና ባለሙያዎች የድሮዋንና የአሁኗን አዲስ አበባ ሲያነጻጽሩ ለውጡ እጅግ ጉልህ እንደሆነ ይመሰክራሉ ብለዋል።

አዲስ አበባ ከኬንያ፣ ከባንግላዲሽና ከፓኪስታን ተርታ አልፋ ቀዳሚ ሆናለች፡፡

ተቋሙ በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች አንጻር የከተማዋን ዕድገት ያነጻጸሩት አዛዡ፣ አሁን ላይ አዲስ አበባ ማንኛውንም ታላቅ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የማስተናገድ ሙሉ ብቃትና አቅም እንዳላት በኩራት ገልጸዋል።

ለዚህም እንደ ኮንቬንሽን ማዕከሎችና ዘመናዊ ሆቴሎች ያሉ መሠረተ ልማቶች መሟላታቸውን ጠቅሰዋል።

በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የቋንቋ እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ወርቅነሽ ተንኮሉ በበኩላቸው፣ የከተማዋ ውበትና ጽዳት ለዜጎችም ሆነ ለውጭ እንግዶች ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ትናንት በጽዳቷና በወንዞቿ እንሳቀቅባት የነበረችው አዲስ አበባ ታሪክ ሆናለች ያሉት ኮሎኔል ወርቅነሽ፣ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ቀይሯታል ያሉት አዛዡ፣ አሁን እንግዶቻችንን የት ልንወስዳቸው ነው ብለን አንጨነቅም፤ ይልቁንም በከተማዋ የምንኮራበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የመጣው ሱዳናዊው ካሊድ አዋስ በበኩሉ፣ በሁሉም አቅጣጫ አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን፣ መንገዶችንና መብራቶችን ተመልክቻለሁ፤ አዲስ አበባ ውብ ሆናለች ሲል አድናቆቱን ገልጿል።

ከኮትዲቫር የመጡት ሌላኛው ሎቲ ሎህ ደግሞ፣ የሥራው ፍጥነት እጅግ አስገራሚ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛሬ ተጀምሮ በሁለት ሳምንት ውስጥ ተጠናቆ ማየት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ምሳሌ ነው ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም በቀጣይ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን አዲስ አበባ ውስጥ እንዲካሄዱና የከተማዋ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲያድግ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review