AMN- የካቲት 18/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ምልክት፣ የአፍሪካ የነፃነት ፋና ተደርጋ ስትጠቀስ ቀዳሚው ምስክር የአድዋ ድል ነው።
ነገር ግን አድዋ የነጭ ወራሪ ድል የተደረገበት የጦር ሜዳ ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም የዛሬው ዘመናዊና ግዙፉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተወለደበት፣ የጥበብና የስትራቴጂ ማህፀንም ጭምር እንጂ፡፡
በ1888ቱ የታሪክ አውድማ ላይ የታየው ሠራዊት፣ እንደ ዛሬው አንድ ወጥ ዩኒፎርምና ማዕከላዊ መዋቅር አልነበረውም። የራስ መኮንን፣ የራስ መንገሻ፣ የራስ ሚካኤልና የሌሎች መኳንንት ጦር ከየአቅጣጫው በመትመም ነበር ኢትዮጵያዊነትን በአድዋ ሰማይ ስር ያሳዩት።

ይህ ሕዝባዊነት ለዛሬው የመከላከያ ሠራዊት ብሔራዊ ስብጥር የጠበቀና ከሕዝብ የወጣ እንዲሆን ለተቀረጸው መርህ ትልቁን ድርሻ አበርክቷል። የአሁኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውልደት ከአድዋ ድል ጋር ያለውን ቁርኝት በተመለከተ በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፍት በስፋት ከትበዋል።
“አድዋ የኢትዮጵያን ነፃነት ከማስከበሩም በላይ፣ የሀገሪቱን ወታደራዊ ተቋም ወደ ዘመናዊነት የመለወጥ ፍላጎት እንዲቀጣጠል ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ነበር።” ሲሉ ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “አድዋ” በተሰኘው መጽሀፋቸው በስፋት ተንትነዋል፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ እንደሚገልጹት፣ ከአድዋ ድል በፊትና በጦርነቱ ወቅት የነበረው ሠራዊት በየአካባቢው ባላባቶችና መኳንንት የሚመራ የነበረ ሲሆን፣ ድሉ ግን አንድ ማዕከላዊ መንግሥት የራሱ የሆነ ቋሚ ሠራዊት የመገንባትን አስፈላጊነት አጉልቶታል። ይህም በሂደት የክልል መኳንንት የጦር ኃይል እየቀነሰ መጥቶ ለብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ቦታ እንዲለቅ መንገድ ከፍቷል።

ዓድዋ የገበሬውን ወታደር ወደ ስልታዊ ተዋጊነት የቀየረ፣ የተበተነ የነበረውን የጦር አመራር ወደ ማዕከላዊ ዕዝ ያመጣና ለዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ መተግበር በር የከፈተ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የልደት ምስክር ወረቀት እንደሆነም የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡
በተጨማሪም የክተት ሥርዓት እንዴት ለብሔራዊ አንድነትና ለሠራዊቱ ጥንካሬ መሠረት እንደሆነ እንዲሁም ማህበራዊና ወታደራዊ ፋይዳውን በተመለከተ አሜሪካዊው የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ ፕሮፌሰር እና የኢትዮጵያ ጥናት ተመራማሪ የነበሩት ዶናልድ ሌቪን “ግሬት ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሃፋቸው በሰፊው አትተዋል፡፡
ሌላው ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆንን ሠራዊት ስንቅና ትጥቅ ማቅረብ የአድዋ ትልቁ ፈተና ነበር። ሆኖም ግን እቴጌ ጣይቱ በዚህ ረገድ የነበራቸው ሚና፣ ለዛሬው የመከላከያ ሎጂስቲክስ ክፍል ቀዳሚ አርአያ ሆኗል። በዘፈቀደ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ ስንቅን ማቅረብ ለጦርነት ድል ግማሹ መንገድ መሆኑ በአድዋ ድል ተረጋግጧል፡፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የክብር ወንበር ላይ እንድትቀመጥ ያደረጋት ሲሆን፣ ይህም ዝና የውጭ ሀገራት ወታደራዊ አማካሪዎች ወደ ሀገር እንዲመጡና ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ወደ ውጭ ሄደው ዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስን እንዲቀስሙ መንገድ ተከፍቷል። በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የሐረር እና የሆለታ ወታደራዊ አካዳሚዎች መመስረት ምክንያት ሆኗል፡፡
ዛሬ ላይ በተደራጀና በዘመናዊ የውጊያ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአድዋ ጀግኖች የደምና የጥበብ ውጤት ነው።
የአድዋ ድል ሀገርን ከወራሪ ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትመካበት ዘመናዊ፣ ቋሚና የሰለጠነ የጥበቃ ኃይል እንዲኖራት ያደረገ የለውጥ ሞተር ሆኖ አልፏል።
በአስማረ መኮንን