ይህቺ የቀድሞዋ አዲስ አበባ አይደለችም፤ በአፍሪካ ምርጥ እና ዘመናዊ የሆነችዉ አዲሷ አዲስ አበባ ነች – ካናዳውያኑ ጥንዶች

You are currently viewing ይህቺ የቀድሞዋ አዲስ አበባ አይደለችም፤ በአፍሪካ ምርጥ እና ዘመናዊ የሆነችዉ አዲሷ አዲስ አበባ ነች – ካናዳውያኑ ጥንዶች

AMN – የካቲት 17/2018 ዓ.ም

ጄትላግ ዋርየርስ የተሰኘዉ ዩቲዩብ ቻናል በመላው ዓለም የጉዞ ይዘቶችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን ስቲቭ እና ኢቫና በተባሉ ካናዳውያን ጥንዶች ይመራል፡፡

ጥንዶቹ የተለመደ ኑሯቸውን በመተዉ ዓለምን ያለገደብ በመዞር ላይ ይገኛሉ፡፡

ይዘት ፈጣሪዎቹ በዋንኛነት ትኩረት የሚያደርጉት በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ ምግቦች፣ ባህል እና በተጓዥነት ህይወት ውስጥ በሚገጥሙ እውነታዎች ላይ ነው።

ጥንዶቹ ሰሞኑን የአፍሪካ መዲና የሆነችዉን አዲስ አበባን የጎበኙ ሲሆን በመዲናዋ እድገትና ልማት በመደነቅ “ይህቺ የቀድሞዋ አዲስ አበባ አይደለችም፤ በአፍሪካ ምርጥ እና ዘመናዊ የሆነችዉ አዲሷ አዲስ አበባ ነች” ሲሉ የተሰማቸዉን ስሜት ለተከታዮቻቸዉ አጋርተዋል፡፡

”አዲስ አበባ በሁሉም መስክ በአፍሪካ ቀዳሚዋ መዲና ነች፤ የአፍሪካ አዲስ ገጽታ” “አዲስ አበባ ውብ ጎዳናዎች አሏት፤ የእግረኛና የሳይክል መስመር ተሰርቶላቸው፣ በአረንጓዴ ልማትና በአበቦች አጊጠው ለእግር ጉዞ እና ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እጅግ ምቹ ሆነዋል” ሲሉ አድናቆታቸዉን ተቀባብለዉ ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ ወደሚገኙ ካፊቴሪያዎች ጎራ በማለት ባህላዊ ምግቦችን በመመገብ እና ቡና በመጠጣት የኢትዮጵያዊያንን መስተንግዶ አድንቀዋል፡፡

ከልጃቸዉ ጋር በመሆን ወደ ሳይንስ ሙዚየም ያቀኑት ካናዳውያን ጥንዶች “ የእግር ኳስ ስቴድየም የሚመስለዉ የሳይንስ ሙዚየም እጅግ በጣም አስደሳች ነዉ፤ ከሌሎች ሙዝየሞችም የተለየ ነዉ፡፡” ሲሉ ገልጸዉታል፡፡

“በመዲናዋ በተለያዩ ቦታዎች ግዙፍ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነዉ፤ እየተገነቡ ያሉት ሕንጻዎች ልዩ ናቸዉ፤ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት የተለየ ነዉ “ ሲሉ ስቲቭ እና ኢቫና ተናግረዋል፡፡

“የአዲስ አበባ ፓርኮች ልዩ ናቸዉ፤ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በቀንና በምሽት ይዝናናሉ፤ አረንጓዴ ተክሎችን ማየት በጣም ያስደስታል፤ ወንዞቹ ንጽህና ማራኪ ናቸዉ፤ ህንጻዎቹ በኢትዮጵያ ባንዲራ አጊጠዋል፤ ምሽት ላይ አዲስ አበባ በጣም ታምራለች፤ ፋዉንቴኖቹና መብራቶቹ ልዩ ናቸዉ፤ ዘመናዊዋን ኢትዮጵያ እያየን ነዉ“ ሲሉ አግራሞታቸዉን ገልጸዋል፡፡

ከልጃቸዉ ጋር በመሆን አዲስ አበባን ተዘዋዉረዉ የጎበኙት ካናዳዊያኑ ጥንዶች “አዲስ አበባን በመጎብኘታችን ተደስተናል፤ ተመልሰን እንደምንመጣም ጥርጥር የለንም“ ብለዋል፡፡

በሄድንበት ሁሉ ሰዉ አክባሪና ተግባቢ ህዝብ አይተናል፤ ከተማዋ በጣም ንጹህ ነች፤ አዲስ አበባ ከጥቂት አመታት በኋላ በአፍሪካ ዘመናዊ እና ምርጧ ከተማ ልትሆን ትችላለች” ሲሉ ያላቸዉን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ እያስመዘገበች ያለዉ ፈጣን እድገት ዛሬም የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ እንደቀጠለ ነዉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review