AMN የካቲት 19/2018 ዓ.ም
የከተማ አስተዳደሩ ለኢንዱስትሪዎች ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በዓለምአቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ምርቶችን ማምረት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አስመልክቶ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚሰሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ተሳተፈዋል፡፡
ጉብኝቱም አምራች ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያገኙት እድልና እያጋጣማቸው ያሉ ችግሮችን መለየት አላማ ያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎችም የማምረት አቅም የሚበረታታ መሆኑን ነው አቶ ጃንጥራር የገለጹት፡፡
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተሰጠው ትኩረትና ድጋፍ ተኪ ምርትን የማምረት አቅም እያደገ መጥቷል ያሉት አቶ ጃንጥራር አሁንም የማምረት አቅምን ለማሳደግና ገበያውን ተደራሽ ለማድረግ አምራቾች መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 66.3 በመቶ መድረሱን ገልጸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አራት አመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገው ድጋፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምን ማሳደግና የስራ እድል ፈጠራን ማስፋት አስችሏል ያሉት ሚኒስትሩ አሁንም አምራች ኢንዱሰትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
5ኛው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽ ማዕከል ባለፈው ቅዳሜ መከፈቱ ይታወሳል፡፡
በፍቃዱ መለሰ