AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም
የ1888ቱ የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ከማድረጉም ባለፈ፣ በባርነት ቀንበር ስር ለነበሩ ሕዝቦች የነፃነት ተስፋን የጫረ ታሪካዊ ክስተት ነው።
በዚህ ታላቅ ድል ውስጥ የኢትዮጵያ ሴቶች የነበራቸው ሚና በቤት ውስጥ ሥራ ብቻ የተወሰነ አልነበረም።
ከዲፕሎማሲያዊ ብልሃት እስከ ግንባር ውጊያ፣ ከቁስለኛ እንክብካቤ እስከ ሞራል ቀስቃሽ ግጥሞች ድረስ ያደረጉት ተሳትፎ የድሉ ዋነኛ ምሰሶ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
የታሪክ ምሁሯ ፍቅርተ መንገሻ እንደሚናገሩት፣ ሴቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት ስንቅና ትጥቅ በማዘጋጀት እንዲሁም ቁስለኞችን በመንከባከብ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
“አድዋ ያለ ሴቶች አሁን እንዳለው ታሪኩ ላይወራ ይችላል” የሚሉት ምሁሯ፣ ሴቶች ባሎቻቸውን፣ አባቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን ወደ ጦር ግንባር በመላክ ብቻ ሳይወሰኑ፣ እህልና የማብሰያ ቁሳቁሶችን በጉልበታቸው ተሸክመው ረጅም መንገድ በመጓዝ ወታደሩ እንዳይራብ አድርገዋል።

ከዚህም ባለፈ ጦርነቱ ሲጀመር የሞቱትን በመቅበር፣ የተጎዱትን በማከም፣ አልፎ ተርፎም መትረየስና መድፍ ተኩሰው እስከመዋጋት የደረሰ ጀግንነት መፈጸማቸውን ታሪክ ያስረዳል።
የአድዋ ጦርነት መንስኤ የነበረውን የጣሊያኖችን ተንኮልና የተሳሳተ አካሄድ ቀድመው የተረዱት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ነበሩ።
ምሁሯ እንደሚገልጹት፣ ጣይቱ በጣሊያንኛ የተጻፈውን ውል በአማርኛ ተተርጉሞ እንዲቀርብ በማድረግ የመጀመሪያውን የጥንቃቄ እርምጃ ወስደዋል።
ጣይቱ ብጡል የጦርነቱ ተሳታፊ ሴቶችን ከማስተባበር ባለፈ፣ ራሳቸው በፈረስ ላይ ሆነው ጦሩን በመምራትና በማዋጋት ረገድ የአድዋ ዋነኛ የድል ሰው መሆናቸውን አስመስክረዋል።
በጦርነቱ ወቅት የሴት አዝማሪዎች ሚናም ከፍተኛ ነበር። ዋሽንት ይዘውና ወገባቸውን ታጥቀው በፉከራ፣ በሽለላና በግጥም ጦሩን በማነቃቃት ወኔ ይዘሩ ነበር። ይህ የሞራል ድጋፍ ወታደሩ ለሀገሩ በቆራጥነት እንዲዋጋ ትልቅ ግብዓት ሆኗል።

የአርበኛ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ብርነሽ መላኩ በበኩላቸው፣ ሴቶች በጦር ሜዳ ከመሳተፍ ባሻገር የአርበኛ ቤተሰቦችን በመንከባከብ ሀገራዊ ግዴታቸውን ይወጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እናቶቻችን መሳሪያቸውን ይዘው ጠላትን የማረኩ ጀግኖች ናቸው የሚሉት ወይዘሮ ብርነሽ፣ ሴቶች ከወንዶች እኩል ተዋግተው ሀገራቸውን ለማዳን የበቁ የሰው ወርቅ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኟ ወይዘሮ ሕይወት አዳነ፣ የአድዋ ድል የሰው ልጅ ሰብዓዊነትና ማንነት የተመዘነበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ጀግና ሴቶች ትላንት መስዋዕትነት የከፈሉት ለዛሬው ትውልድ የማንነት ጥንካሬና ወኔ እንዲሆን ነው ብለዋል።
ይህ የታሪክ አሻራም የአሁኑን ጠላት የሆነውን ድህነትና ኋላ ቀርነትን ድል ለማድረግ እንደ ትልቅ የሞራል ምንጭ ሊያገለግል እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ