AMN- የካቲት 20/2018 ዓ.ም
የጨጓራ ህመም (Gastritis) በአሁኑ ወቅት በብዙዎች ዘንድ የተለመደ የጤና እክል እየሆነ መጥቷል።
ምንም እንኳን ህመሙን በዘላቂነት ለመፈወስ የሚረዱ የህክምና አማራጮች እና የመድኃኒት አይነቶች በሳይንሳዊ መንገድ ተለይተው የሚታወቁ ቢሆንም፣ ብዙ ሕመምተኞች ግን የማቃጠል እና ሌሎች ስሜቶችን ለጊዜው ለማስታገስ ብቻ ትኩረት ሲሰጡ ይስተዋላል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና ክፍል የጉበት፣ የአንጀት እና የጨጓራ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሚፍታህ ደሊል ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ብዙዎች የጨጓራ ህመምን እንደ ቀላል የሆድ መነፋት ወይም ቃጠሎ በመቁጠር ችላ ቢሉትም፣ ችግሩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ የጨጓራን ሽፋን እስከ መቅደድና ለከፍተኛ ደም መፍሰስ ሊዳርግ ይችላል።

የጨጓራ ህመም የሚከሰተው በጨጓራ የውስጠኛው ሽፋን ላይ ቁስለት ወይም እብጠት ሲፈጠር መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሚፍታህ፣ ለዚህም ዋነኛው መንስኤ ኤች ፓይሎሪ የተባለ ባክቴሪያ መሆኑን ወይም በሀኪም ያልታዘዙ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ለረጅም ጊዜ መውሰድ የህመሙ መንስኤ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ህመሙ ሲጀምር በሆድ የላይኛው ክፍል ላይ የማቃጠል ስሜት፣ የምግብ አለመፈጨት እና የማቅለሽለሽ ምልክቶችን የሚያሳይ ቢሆንም፣ እነዚህ ምልክቶች ከአንድ ሳምንት በላይ ከቆዩ ግን አፋጣኝ የህክምና ክትትልን የሚሹ መሆናቸውን ባለሙያው አስረድተዋል።
በተጨማሪም የምግብ ፍላጎት መቀነስና ያለምክንያት የሰውነት ክብደት መቀነስ ካጋጠመ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
በሽታው እንዳይባባስና ወደ ካንሰር ደረጃ እንዳይሸጋገር የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ቀዳሚው መፍትሔ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሚፍታህ፣ በቀን ሶስት ጊዜ በብዛት ከመመገብ ይልቅ መጠናቸው አነስ ያሉ ምግቦችን በየመሃሉ መውሰድ የጨጓራ አሲድ በቁስለቱ ላይ የሚያደርሰውን ጫና እንደሚቀንስ አስረድተዋል።

ከበሽታው ለማገገም ቅመም የበዛባቸውን፣ በዘይት የተጠበሱና አሲድነት ያላቸውን ምግቦች ማስወገድ።
የጨጓራን የመከላከል አቅም የሚያዳክሙ እንደ አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ ያሉ ልማዶችን ማቆም እንደሚገባ ዶ/ር ሚፍታህ መክረዋል።
ደም የቀላቀለ ትውከት ወይም የሰገራ ቀለም ወደ ጥቁርነት መለወጥ የታየባቸው ሰዎች የጨጓራ ደም መፍሰስ ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ሳይዘገዩ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባቸውም አስረድተዋል።
ለጨጓራ ህመም ከሚሰጡ መድኃኒቶች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት የጨጓራ ባክቴሪያን ለማጥፋት የሚረዱ የአንቲባዮቲክ ጥምረቶች መሆናቸውን ዶክተር ሚፍታህ ገልጸው፣ እነዚህ መድኃኒቶች ባክቴሪያው በጨጓራ ሽፋን ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት በመቀልበስ ቁስለት እንዳይፈጠር ይከላከላሉ ብልዋል።
ይሁን እንጂ መድኃኒቶችን ሀኪም ባዘዘው መመሪያ መሰረት እስከ መጨረሻው አለመጨረስ ባክቴሪያው መድኃኒት እንዲላመድ ስለሚያደርገው፣ ታካሚዎች መድኃኒቱን በአግባቡ በመጨረስ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው