AMN – የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም
የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና በሆነው የአድዋ ጦርነት ወቅት፣ ለታሪካዊው ድል መመዝገብ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ተሳትፎዎች መካከል ኪነ-ጥበብ ቀዳሚው ነው።
የአድዋ ጀግኖች ከመላው ኢትዮጵያ ያለ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ እና ቋንቋ ልዩነት ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ሲሰለፉ፤ ወኔን ለመቀስቀስ፣ ጽናትን ለማላቅና ጠላትን ለማንበርከክ ፉከራ፣ ቀረርቶና ሽለላን እንደ ስልታዊ መሣሪያ ተጠቅመዋል።
ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ፣ ጋሻና ጎራዴ በመታጠቅ በግርማ ሞገስ የሚቀርቡት እነዚህ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ወገንን ከማጀገናቸው ባለፈ፣ በወራሪው የጣሊያን ጦር ዘንድ ፍርሃትንና መሸበርን ፈጥረው እንደነበር የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ።
ጀግኖቹ ከጦርነቱ በፊት፣ በጦርነቱ ወቅትና ከድሉ በኋላም በጋራ ፎክረዋል፤ ተንጎራድደዋል፤ በጋራም አሸንፈዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር አባላት የሆኑት ኮሎኔል አዳነ ቶሌራ እና መቶ አለቃ ጉደታ ገልሜሳ እንደሚመሰክሩት፣ የአድዋ ጀግኖች ከምንም በላይ ሀገራዊ ፍቅርንና ነፃነትን በማስቀደም፣ በጥበብ የታጀበ የማይናድ ታሪክ ሰርተዋል።

ዛሬ ላይ ታዋቂ ድምፃውያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚዜሟቸው ሽለላዎችና ፉከራዎች የአድዋ ጀግኖች ለቀጣዩ ትውልድ ያወረሱት የወል ቅርስ ነዉ፡፡
ይህንን ታላቅ እሴት ለማውረስም የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ የአብርሆት የኪነ-ጥበብ መድረክን በሜክሲኮ አደባባይ በድምቀት አከናውኗል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሉባባ ጀማል እንደገለጹት፣ የአድዋ ድል የጥበብም ድል ጭምር በመሆኑ፣ አዲሱ ትውልድ ከአድዋ ጀግኖች ለሀገራዊ ጥቅም በጋራ መቆምንና አብሮነትን ሊማር ይገባል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተገነቡ ዘመናዊ የኪነ-ጥበብ ማዕከላትና ፕላዛዎች መዲናዋን ለዘርፉ ምቹ አድርገዋታል። የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም ይህንን ዕድል በመጠቀም ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ሊያቀርቡ ይገባል።
የአድዋ ጀግኖች አንድነታቸውን ሊያሳጡ የመጡ ወራሪዎችን በጋራ እንደመከቱ ሁሉ፣ የዘመኑ ትውልድም በሀገር ላይ የሚቃጡ እኩይ ድርጊቶችንና ድህነትን በጋራ ሊፋለም እንደሚገባ መልዕክት ተላልፏል።
ዛሬም እንደ ትላንቱ ጥበብ ለሀገር ህልውና ትልቅ ምሰሶ መሆኗ በአድዋ ተመስክሯል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ