የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫዎች ስነ ጥበባዊ በሆነ መልኩ መሰራታቸው አሰባሰቢ ትርክት ለመገንባት እንደሚያግዙ ተጠቁሟል
ኢትዮጵያ በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅባቸው በርካታ መገለጫዎች አሏት፡፡ ጥንታዊነቷ፣ የሰው ዘር መገኛነቷ፣ በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቀች ብቸኛ ሀገር መሆኗ፣ የቀን አቆጣጠሯንና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል። ብዝሃነቷም ሌላው መለያዋ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያ ብሔርን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ ሃይማኖትን፣ ቋንቋን ጨምሮ የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ሀገር ናት፡፡ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ በጋራ በመቆም መመከት ደግሞ የኢትዮጵያዊውያን የጋራ ማንነት መገለጫ ነው፡፡ በየዘመናቱ ከውጭ ወረራ ሲያጋጥማቸው በአንድነት ሆኖ አሳፍሮ በመመለስ የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ነጻነት አስጠብቀውና አጽንተው ዘልቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ የዓድዋ ድል ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ኢብራሂም ሙሉሸዋ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገልፁት፣ የዓድዋ ድል በአራቱም አቅጣጫ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የአመለካከት፣ የጾታና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድባቸው የዳግማዊ አፄ ምኒልክን የክተት አዋጅ በመቀበል ጠላትን ለመፋለም በጋራ የተመሙበት፤ የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና አንድነት ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ልዩነት እንኳን ቢኖራቸው ሀገር ችግር ሲገጥማት ወይም ስትደፈር እንዴት በአንድነት ጠላትን ለመከላከል እንደሚሰለፉ የታየበት ድል ነው፡፡
ተክለጻድቅ መኩሪያ “ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ” በሚለው መጽሀፋቸው ላይ፣ የአካባቢው መሳፍንት (አስተዳዳሪዎች) “…ዳግማዊ ምኒልክን እንደሸዋ ንጉስና እንደባዕድ ቆጥረው የራሳቸውን ምኞት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለመፈፀም በመሞከር ተለይተው ቢሆን ኖሮ ወይም እንሸፍት ብለው የውስጥ ግጭት ተነስቶ ቢሆን ኖሮ የጣሊያን ጦር ምን ያህል ይጠቅመው እንደነበር ግልፅ ነው። የጣሊያን የጦርና የፖለቲካ መሪዎች ውስጥ ለውስጥ እየተላላኩ ጆሯቸውን ከፍተው የጠበቁት ይህንን ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ አንድነት፣ የመኳንንትና የመሳፍንቱ ህብረት፣ የጦር ሰራዊቱ ታማኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የጠበቀ ነበር” ሲሉ ለድሉ መገኘት የኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም የነበረውን ሚና አመላክተዋል፡፡
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በጦርነቱ ጣሊያን በማይቀለበስ መልኩ ሽንፈት ከደረሰባት በኋላ በአዲስ አበባ ስምምነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት እውቅና ሰጥታለች፡፡ ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮችም የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማክበር ቃል ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓድዋ ባስመዘገበችው ድል ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማእከል ልትሆን እንደቻለች የታሪክ ተመራማሪው ኢብራሂም (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
እንደ ዓድዋ ያሉ ታሪኮች ለጋራ ትርክት ግንባታ እንዴት እንጠቀምባቸው?
ትርክት መግባባትና አንድነትን ማጠናከሪያ አሊያም ልዩነቶችን በማስፋት ወደ ግጭት የሚያስገባ መሳሪያ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳና በረከት” በሚለው መጽሀፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ ህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም እና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ተቃራኒ ትርክቶች ይራመዳሉ፡፡ እነዚህም አንድነታችንና አብሮነታችን እንዳይጠናከር፣ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንዘፈቅ አድርገውናል፡፡
በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በነበሩት ሶስት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሲቀነቀን የነበረው ነጠላ ትርክት በማህበረሰብ፣ በሊሂቃን መካከል መከፋፈል፣ ቅራኔ፣ አለመተማመን እንዲባባስ በማድረግ የሀገር ግንባታው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን በጂማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ኑሩ ይማም ይናገራሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የጋራ ትርክት መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ የጋራ ድሎች፣ የጋራ ቅርስ፣ ብዝሃ ባህል ሀብቶችን በመለየት የትርክት ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ገበታ ለሸገር በተሰሩ የአንድነትና የእንጦጦ ፓርኮች እና የወዳጅነት አደባባይ እንዲሁም ደግሞ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ እና ሌሎች ልማቶች የኢትዮጵያን መልክና ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት የሚያሳዩ መገለጫዎች በቅርፃ ቅርፅ፣ በስዕል፣ በጽሑፍና በተለያየ ስነ ጥበባዊ ቅርፅ ሳቢ በሆነ መልኩ ተካትተው ተሰርተዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የጋራ የድልና የከፍታ ምልክት ከሆኑ ታሪኮች መካከል ዋነኛው ዓድዋ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካና ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ችቦ ብርሃን የለኮሰ፤ የዓለም ታሪክን የቀየረውን ድል በልኩ መዘከር እንዲቻል በአዲስ አበባ እምብርት ግዙፍ መታሰቢያ ተገንብቷል፡፡
በወንዝ ዳርቻ ልማትም ለምሳሌ ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ በተሰራው የወንዝ ዳርቻ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ወረድ ብሎ የዓድዋ ዘማቾች የተሰባሰቡበት ቦታ አካባቢ፣ የሀገርን ዳር ድንበርና ነፃነት ለማስከበር ኢትዮጵያውያን ስንቅና የጦር መሳሪያ በፈረስ ላይ ሆነውና ጭነው፣ ጀግኖች አርበኞች ጋሻና ጦር ይዘው ጉዞ ሲያደርጉ የሚያሳዩ ሐውልቶች ቆመውና በግድግዳ ላይ በስዕል ተስለው ይታያሉ። ፈረሶች እንዲሁም ተራራማ በሆነው መልክአምድር የሚኖሩ ብርቅዬ ጭላዳ ዝንጀሮዎች በልዩ የስነ ጥበብ ተሰርተው ይታያሉ፡፡
ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ መተላለፊያ በሆነውና በዓድዋ ጦርነት ከተሳተፉ የጦር መሪዎች አንዱ በሆኑት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተሰየመው ጥንታዊ “የራስ መኮንን ድልድይም” ከጎን የመስታወት ድልድይ፣ ጀግኖች አርበኞች ይጠቀሙባቸው የነበሩ እንደ ጋሻና ጦር ያሉ ምልክቶችን አካትቶ በሚያምር ስነ ጥበባዊ ውበት ታድሶ ተሰርቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ፡- የወንዝ ዳርቻ” በሚል ርዕስ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከወራት በፊት በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ላይ እንደተናገሩት፣ በአራዳ ፓርክ የዓድዋ ዘማቾችን ታሪክ የሚያሳዩ ሐውልቶች እንዲቆሙ የተደረገው ለቱሪስት መስህብነትና ትውልድ እንዲማርባቸው ታስቦ ነው፡፡ “ታሪካችንን ማቅለል አይገባንም፡፡ የጋራ ትርክት መገንቢያችን ነው፡፡ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን፣ ሀይል፣ አቅምና ሀሳባቸውን በማሰባሰብ ሀገራቸውን የታደጉበት፣ ዛሬ የምንኮራባትን ሀገር ያስረከቡን አበውና እመው በምን ሚስጢር ነው? የሚለውን ትውልዱ የሚማርበትን ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ልክ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ ተሰባስበው ከጣሊያን ጋር በመፋለም ያስገኙት ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል ሁሉም የተሳተፈበት መሆኑ እንዲታወቅ መደረጉ እንደሀገር የጋራ የሆነ ስነ ልቦናዊ አንድነት እንዲኖረን ያደርጋል። ይህም የኢትዮጵያውያን አንድነትና ሰላም እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡ የሀገር ኢኮኖሚ ያድጋል፡፡ በሀገር ላይ አደጋ ሲፈጠር በጋራ የሚቆም ህዝብ ይፈጥራል ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ኢብራሂም (ዶ/ር) ድሉን መዘከር የሚያስገኘውን ጥቅም ያስረዳሉ፡፡
የታሪክ መምህር ኑሩ ይማም በበኩላቸው በአዲስ አበባ አዳዲስ በተገነቡና በታደሱ ሙዚየሞች፣ በኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በፓርኮች የኢትዮጵያውን ማንነት መገለጫዎችን፣ ታሪኮችንና ጀግኖችን ስነ ጥበባዊ በሆነ መልኩ መሰራቱ አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል። አዲስ አበባን ውብና ፅዱ እንድትሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ከውጭ ሀገር የመጣ ቱሪስት አዲስ አበባን ሲጎበኝ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችን፣ ምልክቶችን፣ ታሪካዊ ሁነቶችን በቀላሉና በአጭር ጊዜ መረዳት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በአንድ ቦታ ብዙ ታሪኮችን በአንድ ቦታ መረዳት እንዲችሉ በማድረግ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ እንዲከባበሩና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በር ይከፍታል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ኢብራሂም በበኩላቸው የጋራ ትርክት ለመገንባት የጋራ የሆኑ ታሪኮችን በአግባቡ በጥናትና ምርምር በመለየት አጉልቶ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በእድር፣ እቁብ፣ ሰርግ፣ ለቅሶ በመደጋገፍና በመረዳዳት ሲኖሩ የጋራ እሴት ገንብተዋል፡፡ እነዚህን በማጉላትና በመጠበቅ ለጋራ ትርክት ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የሁሉም ኩራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ በኢትዮጵያውያን መነሳሳት፣ ሌሎች የጋራ ነገሮችን አብሮ ለመጀመርና የጋራ ትርክት ለመገንባት ጥሩ መነሻ ይሆናል፡፡ የጋራ ትርክትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሚረዳ ታምኖበት እየተሰራበት ያለው ሀገራዊ የምክክር መድረክም በሀገራችን ህዝቦች መካከል ለልዩነት ምክንያት የሆኑ፣ አብሮነትን እየፈተኑ ያሉ ቅራኔዎችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ብሔራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ