ዓድዋ – የጥቁር ሕዝቦች የድል መዝገብ እና የትውልድ ኩራት

You are currently viewing ዓድዋ – የጥቁር ሕዝቦች የድል መዝገብ እና የትውልድ ኩራት

AMN- የካቲት 22/2018 ዓ.ም

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ነው።

ይህንን ታላቅ ታሪክ የሚመጥን የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ፣ የታሪካችንን ክብር ከፍ የሚያደርግና የትውልድ ኩራት መሆኑን ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ ገልጸዋል።

ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ወራሪው የጣሊያን ኃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደፈረ ጊዜ አፄ ምኒልክ “ጠላት ፈጣሪ የሰጠንን የባህር በር አልፎ ገብቷል” በማለት የክተት አዋጅ ማወጃቸውን አስታውሰዋል።

ይህንን ጥሪ የሰሙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከየአቅጣጫው “እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ” በመሆን ወደ ዓድዋ መትመማቸውን አቶ ጥበቡ ገልጸዋል።

ጠላት ኢትዮጵያውያንን መሣሪያ የሌላቸውና ኋላ ቀር አድርጎ ቢገምታቸውም፣ እውነታው ግን ፈጽሞ የተለየ እንደነበር አቶ ጥበቡ ያብራራሉ።

ከተለያዩ ክፍለ ሀገራት የሚመጣውን እጅግ ግዙፍ ሠራዊትና ስንቅ የማስተባበሩ ሥራ፣ በወቅቱ ለነበረው ዓለም አስደናቂ የሆነ የሎጂስቲክስ ስኬት ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ዛሬ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ይህንን ሁሉ ገድል በዝርዝር ለዓለም የሚያሳይ መሆኑን አቶ ጥበቡ አመላክተዋል።

ማንኛውም ጥቁር ሕዝብም ሆነ የዓለም መሪ ወደ በሚመጣበት ጊዜ የሚኮራበትና የሚደነቅበት ታሪካዊ መዝገብ ሆኖ እንደሚያገለግልም አብራርተዋል።

ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የድል መዝገብ በመሆኑ፣ ይህንን ታሪክ በሙዚየሙ ውስጥ በክብር ተቀምጦ ማግኘት ትልቅ ትርጉም እንዳለው አቶ ጥበቡ በለጠ በቃለ መጠይቃቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review