AMN የካቲት 22/2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 130ኛውን የዐድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ወደ ዐድዋ የዘመቱ ጀግኖቻችን ሁሉ በሁሉም ነገር የተስማሙ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ዓላማ ነበራቸው እንጂ አንድ ዓይነት አልነበሩም፤ አንድ ሀገር ነበራቸው እንጂ አንድ ባህልና እምነት አልነበራቸውም ብለዋል፡፡
በዚያ ጊዜ ሀገራቸውን ከድተው ከጠላት ጋር ያበሩ ባንዳዎች እና ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ ዘላቂ የሀገራቸውን ጥቅም የሸጡ ምንደኞችም እንደነበሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከባዳ ጋር ወግነው ወገናቸውን ያስማሙ ደላሎችም እንደነበሩም አንስተዋል፡፡
ጀግኖች እናቶቻችን እና አባቶቻችን የተዋጉት ከወራሪው የጣሊያን ጦር ጋር ብቻ አልነበረም። ከምንደኞች፣ ከባንዳዎች እና ከሀገር ደላሎች ጭምር እንጂ ብለዋል፡፡
ዐርበኝነት ማለት ባዳና ባንዳን ማሸነፍ ማለት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ጥቅም ሲባል የግል ጥቅምን ማሸነፍ ማለት ነው። ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ክብር ሲባል የራስን ክብር መሠዋት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዐድዋ ድል በዓል እነዚህን ሁሉ የምናስታውስበት ነው ብለዋል፡፡