AMN የካቲት 26/2018 ዓ.ም
የአፍሪካ መዲና በሆነች አዲስ አበባ ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረጉ በርካታ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች በርካቶችን ተጠቃሚ ከማድረጋቸዉ እና የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየራቸዉም በላይ በአህጉርና አለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ መሰረተ ልማት በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡
መዲናዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተከናወኑ በርካታ የልማት ስራዎችና ሜጋ ፕሮጀክቶች በከተማዋ የሚካሄዱ ኩነቶች ብዛት ጨምሯል፡፡
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ 150 የሚሆኑ አለማቀፍና አህጉር አቀፍ ኩነቶች አዲስ አበባ ላይ ተካሂደዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠዉ ልዩ ትኩረት በቀጣይነት ፍሬ ማፍራት ከጀመሩ የልማት ስራዎች መካከል ዋንኛዉ ሲሆን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ውድድር በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ዕድል አግኝታለች፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርት መሰረተ ልማት በሰጠዉ ልዩ ትኩረት መዲና በዓለም አትሌቲክስ ካላንደር ውስጥ መካተት በመቻሏ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የአለም አቀፍ ግንኙነትና የስፖርት ዲፕሎማሲ እና የስፖርት መሰረተልማት መስፋፋት ስራችን ፍሬ እያፈራ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ ለሀገራችን ብሎም ለአትሌቲክስ ባለሙያዎች ትልቅ እድል ነዉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህ ትልቅ ውጤት እንዲመዘገብ የለፋችሁ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት 32 የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መቻሉም ለስፖርት መሰረተ ልማት የሰጠዉን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡
መሰረተ ልማቶቹም እግር ኳስ ሜዳ ፤ መሮጫ ትራክ ፤ 3በ1 ሜዳ ፤ 2በ1 ሜዳ እና ስኬት ቦርድን ያካትታሉ፡፡
በካዛንቺስ መልሶ ማልማት እየተገነባ ያለዉና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘነዉ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ ስፖርትን የያዘ ስፖርት ፓርክም አዲስ አበባ ከከተማ አልፎ ለአፍሪካ ብሎም ለአለም የምታበረክተዉ ዋንኛዉ የስፖርት መሰረተ ልማት ነዉ፡፡
መዲናዋ በመሰረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በክረምትና በበጋ በርካታ ታዳጊ ወጣቶችን በማሰልጠን ላይ የምትገኝ ሲሆን ተተኪ ስፖርተኞችም በቀጣይ አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚወክሉ ናቸዉ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርትን በማስፋፋት ሁሉንም ዜጎች በአካል እና በአእምሮ ጎልብተዉ ጤናማ እና አምራች እንዲሆኑ በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪዎችን ጨምሮ በመዲናዋ የሚኖሩ ዲፕሎማቶች፤ የዉጭ ሃገር ዜጎችና ቱሪስቶች በሚኖሩበት፣ በሚማሩበት፣ በሚሠሩበት እና በሚዝናኑበት አካባቢ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን በመከወን የአዲስ አበባ የስፖርት መሰረተ ልማት ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡
አዲስ አበባ በንግድ እንቅስቃሴዋ ብቻ ሳይሆን በስፖቱም ዘርፍ ክረምት ከበጋ; በቀንና በምሽት የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚከወኑባት ዘመናዊ መዲና ሆናለች፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ