ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት መመልከታቸዉን ገለጹ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት መመልከታቸዉን ገለጹ

AMN የካቲት 30/2018

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማለዳ በከተማችን ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት ተመልክተናል ብለዋል።

በአጠቃላይ የተመለከትናቸው መንገዶች 8.9 ኪ.ሜ ርዝመት የሚሸፍኑ ሲሆኑ የአውቶቡስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ እና የአየር ጤና – ካራ ወለቴ የአስፓልት መንገድ ግንባታዎች ናቸዉ።

የአውቶቡስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ አዲስ የአስፓልት መንገድ ሲሆን 3.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው፣ በግራና በቀኝ በአጠቃላይ 6 የመኪና መስመሮች (Lanes) ያሉት ሲሆን፣ ሰፊ የእግረኛ መንገድ እና የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃና ፍሳሽ መሠረተ ልማቶች በመሬት ውስጥ መሸጋገሪያ መንገድ(Underpass) ያለዉ፣በ18 አደባባይ ላይ 60 ሜትር ስፋት ያለው መሻገሪያ ድልድይ ( overpass) ይገነባለታል ብለዋል።

እንዲሁም በጦር ኃይሎች መስመር በኩል ያለውን ነባር የቀለበት መንገድ በማስፋት የማሻሻል ስራን ያካተተ ፕሮጀክት ነው።

ሌላኛዉ የተመለከትነዉ የአየር ጤና – ካራ ወለቴ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን 5.6 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ይህ የመንገድ ከተማዋን ወደ ጅማ እና ሆሳዕና ከሚወጣዉ መንገድ ጋር የሚያስተሳስር ፣ ጉዞን ይበልጥ ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸዉ የግባታ ጊዜ አንፃር በመዘግየታቸው የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ሆነው ይነሱ የነበሩ ናቸው። ዋነኛው የቅሬታ ምክንያት የወሰን ማስከበር ችግር የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን በመፍታት ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች በከተማዋ የኮሪደር ልማት ስታንዳርድ የሚገነቡ ሲሆን፣ ሌሎች ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን ጭምር ያካተቱ ሲሆን በፍጥነት ተጠናቅቀዉ ለአገልግሎት እንዲበቁ ክትትላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል።

አሁን በከተማችን አጠቃላይ 140 የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 104ቱ በከተማው መንገዶች ባለሥልጣን በራስ አቅም፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በግል ኮንትራክተሮች እየተገነቡ ይገኛሉ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review