AMM – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም
የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ በትግራይ ክልል ለበርካታ ዓመታት የቆየው ኋላቀር የፖለቲካ አካሄድ ክልሉን ወደ ኋላ ያስቀረ በመሆኑ፣ አዳዲስና አማራጭ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ሊተገበሩ እንደሚገባ ገለጸ።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ባለፉት አሥርት ዓመታት በክልሉ የነበረው ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር የሕዝቡን ሁለንተናዊ አቅም ገድቦ መቆየቱን ገልጸዋል።
አቶ ሀፍቱ አክለውም፣ በትግራይ ክልል ለረጅም ዓመታት የሰፈነው የአንድ ወገን የፖለቲካ አስተሳሰብ ክልሉንና ነዋሪዎቹን አሳስሮ መያዙን አመልክተዋል።
በተለይም ህወሃት ሲከተለው የነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብና መዋቅር የሕዝቡን አንድነት ከመጉዳቱም በላይ፣ ዜጎች የፈለጉትን የፖለቲካ አማራጭ በነፃነት እንዳይከተሉ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ስምረት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት ለክልሉ ሕዝብ አማራጭ የሆኑ የፖለቲካ ሃሳቦችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀፍቱ፤ በቀጣይ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ፓርቲያቸው የሃሳብ የበላይነትን መሠረት በማድረግ እንደሚወዳደር አስታውቀዋል።

ማንኛውም በክልሉ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል በጉልበት ሳይሆን በሃሳብ ሊፋለም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ወጣቱ ትውልድ ካለፈው ጦርነትና የፖለቲካ ቀውስ ወጥቶ ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ እና ለፈጠራ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ክልሉን አሁን ካለበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለማውጣት አዲስና ብልህ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲሁም አመራር እንደሚያስፈልግም አቶ ሀፍቱ ጨምረው ገልጸዋል።
በመጨረሻም ፓርቲው በክልሉ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲሰፍንና የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሪፎርሞች እንዲተገበሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
በበረከት ጌታቸው