AMN – መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ምክንያት ከመሥሪያ ቦታቸው የተነሱና የንግድ ቦታ የመገንባት አቅም ያልነበራቸው ነጋዴዎች፣ በመንግሥት የተገነቡ የንግድ ሱቆችን በዕጣ ተረከቡ።
ቀደም ሲል የቀበሌ ወይም የመንግሥት ንግድ ቤቶችን ተከራይተው ይሠሩ የነበሩ እነዚህ የልማት ተነሺዎች፤ በአክሲዮን ተደራጅተው የንግድ ሕንፃ እንዲገነቡ ዕድል ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፤ በርካታ ነዋሪዎች ግን የሊዝ ክፍያ የመክፈልና የመገንባት አቅም ስላልነበራቸው ጥያቄያቸውንና ቅሬታቸውን ለአስተዳደሩ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ በአክሲዮን መቀጠል ያልቻሉና አቅም የሌላቸውን ነጋዴዎች ዝርዝር የእያንዳንዱን ማህበር ቃለ-ጉባዔ በመመርመር ለይቷል።
በዚህም መሠረት በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻና በመልሶ ማልማት ሥራዎች ለተነሱ ነዋሪዎች ምትክ የንግድ ሱቆች እንዲሰጡ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የነዋሪዎቹን ችግር አዳምጠው መንግሥት በገነባቸው የቀበሌ ንግድ ቤቶችና በኮሪደር ልማት በተገነቡ ሱቆች ውስጥ ተከራይተው እንዲሠሩ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልጸዋል።
ለነዚሁ ተነሺዎች እንዲተላለፉ የተወሰኑት 315 የንግድ ሱቆች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ባለባቸው ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 249ኙ በልደታ ክፍለ ከተማ አፍሪካ ሕብረት አካባቢ በተገነባው የገበያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ቀሪዎቹ 66 ሱቆች ደግሞ በአቃቂ ገበያ ማዕከል ውስጥ የተገነቡ መሆናቸው ታውቋል።

ከዕጣ ባለዕድለኞች አንዱ የሆኑት አቶ አምዱ ከድር፣ ዕድሉ በመድረሱ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ጠንክረው በመሥራት ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን እንደሚጠቅሙ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ባለዕድለኛ ወይዘሮ አመለወርቅ አበበ በበኩላቸው፣ ለ45 ዓመታት በጀበና ቡናና በቁርስ ንግድ ሲተዳደሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ አሁን የተረከቡትን ሱቅ በጥናት ላይ ተመስርተው ለተሻለ ሥራ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።
የእድሉ ተጠቃሚ አቶ ሰኢድ ሀሰን በሰጡት አስተያየት፣ ነጋዴዎቹ ለልማት ሲሉ ከመኖሪያቸውና ከመሥሪያ ቦታቸው ተነስተው ሲጉላሉ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ የከተማ አስተዳደሩ ሱቆችን ገንብቶ ማስረከቡ ትልቅ ተስፋና ለውጥ መሆኑን አመልክተዋል።
በታምራት ቢሻው