AMN መጋቢት 16/2018
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት ለተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማነት የብድርና ቁጠባ ተቋማት ሚናቸውን የመወጣት ድርብ ሃላፊነት እንዳለባቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር የፋይናንስ አቅርቦት፣ አካታችነትና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ ዓለምአቀፍ ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እያካሄደ ነው። ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የዘርፉ ተዋንያን፣ ባለሙያዎች የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የብድርና ቁጠባ ተቋማት የአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት አቅም እንዲጨምር ዓይነተኛ ሚና አላቸው።
የሴቶች፣ የወጣቶችና አርብቶ አደር አካባቢ ያሉ ማህበረሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ላይ ቁልፍ ድርሻ እንዳላቸውም አብራርተዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍ ያለ ሚና አላቸው ያሉት ገዥው፤ የድህነት ቅነሳ ተግባራት እንዲሳኩና ብልፅግና እውን እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
ተቋማቱ ለበርካታ ሚሊዮን ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆኑ የዕድገት አጋሮች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሳለጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡