AMN — መጋቢት 20 /2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያከናወናቸው የኮሪደር ልማት በርካታ ውጤት ማሳየት ጀምረዋል።
ከእነዚህም መካከል በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ዘመናዊ የታክሲ መጫኛና መውረጃ ተርሚናሎች ለተሳፋሪዎችና ለዘርፉ ተዋናዮች ከፍተኛ እፎይታ እየፈጠሩ መሆኑን ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በከተማዋ ባልተማከለ የትራንስፖርት ሥርዓት ምክንያት ተሳፋሪዎች ለከፍተኛ እንግልት ይዳረጉ እንደነበር የአይን እማኞች ይናገራሉ።
አስተያየታቸውን ለኤ ኤም ኤን የሰጡት አቶ ተስፋዬ ፈለቀ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በየመንገዱ የሚደረጉ የታክሲ ማቆሚያዎች ለተሳፋሪዎች ደህንነት አስጊ ከመሆናቸው ባለፈ ለስርቆትና ላልተገባ መጉላላት ያጋልጡ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን የፀሃይ እና ዝናብ መከላከያ ቦታዎች አረፍ በማለት ስልካችንን ቻርጅ እያደረግንና በሥርዓት ተሰልፈን አገልግሎት ማግኘት ችለናል ሲሉ ለውጡን አስረድተዋል።
ሌላው ተጠቃሚ አቶ ንጋቱ አቸነፍ፤ ተርሚናሎቹ መገንባታቸው በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነስ ረገድም የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ታክሲዎች መንገድ ላይ ቆመው የሚጭኑበት አሠራር ቀርቶ ወደ ተርሚናል መግባታቸው የትራፊክ ፍሰቱ እንዲቀላጠፍና አላስፈላጊ እንግልት እንዲቀንሱ ረድቷል ሲሉም አክለዋል።
በተለይም እንደ ሜክሲኮ እና መገናኛ ባሉ ተርሚናሎች ትላልቅ መናኸሪያዎች አካባቢ ይስተዋል የነበረው የስርቆት ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አቶ ተዋበ አንለይ ገልጸዋል።
የታክሲ መጫኛ ቦታዎች በግልጽ መታወቃቸው ለተሳፋሪው ትልቅ ዋስትናና መተማመኛ መፍጠሩንም አክለዋል።
የታክሲ አሽከርካሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ምንም እንኳን የተርሚናሎቹ መገንባት እንደ ትልቅ ስኬት ቢነሳም፣ በቀጣይ ሊሟሉ የሚገባቸው መሠረተ ልማቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በተለይም የተሳፋሪዎችን ምቾት ሙሉ በሙሉ ለመጠበቅ በቂ የመጸዳጃ ቤቶችና የመጠለያ አቅርቦቶች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ መሰል የዘመናዊ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማስፋፋት አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
በበረከት ጌታቸው