AMN – መጋቢት 24/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የገጠሟትን ውስብስብ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች በጽናት በመቋቋም ሉዓላዊነትንና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ተጨባጭ ውጤቶች ማስመዝገብ ችላለች።
በተለይም በኢነርጂ፣ በባህር በር ፍላጎት እና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘርፎች አዳዲስ ምዕራፎችን መክፈት የቻለችባቸው ስኬታማ ዓመታት ሆነው ተመዝግበዋል።
በኢነርጂው ዘርፍ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሻራ ያረፈበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት፣ የሀገሪቱን የኃይል ዋስትና የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ይህም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትንና ቀጣናዊ ትስስርን የምታጠናክርበትን ዕድል ፈጥሯል።
የግድቡ መጠናቀቅ በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ተደራዳሪነት ከማሳደጉም በላይ፣ የውሃ ሀብቷን የማልማት ተፈጥሯዊ መብቷን በተግባር ያረጋገጠ ስኬት ሆኗል።
የባህር በር ፍላጐቷን እውን ለማድረግ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ ጥረቶች ባለፉት የለውጥ ዓመታት ወደ ተጨባጭ ተግባራዊ ንቅናቄ ተሸጋግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን እንደ አንድ የብሔራዊ ደህንነትና የህልውና ጉዳይ አድርጋ በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ማድረግ ችላለች።

በተለይም የባህር በር ፍላጎቷን በንግግርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማሳካት የጀመረችው እንቅስቃሴ፣ ለዘመናት ታፍኖ የነበረውን ጥያቄ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲያገኝ እየተሰራበት ይገኛል።
ይህም የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ ወጪ ለመቀነስ፣ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥና የባህር ኃይልን በመገንባት ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት አዲስ ከፍታ ላይ የሚያደርስ ነው።
እነዚህ ድሎች ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን መሪነት ከማረጋገጣቸውም በላይ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራና የማይናወጥ ብሔራዊ መሠረት የጣሉ እንዲሆኑ ታስቦ እየተሰራ ነው ።
በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡት እነዚህ ሁለንተናዊ ስኬቶች ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለታላቅነት የምታደርገውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው።
በበረከት ጌታቸው